
ሰቆጣ: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን እለት በማስመልከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀት በዓልን ወደ ወንዝ በመውረድ ታከብራለች።
በዚህም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ጥምቀተ ባሕሩን በባረኩበት ወቅት አባታዊ ምክር ያሥተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ የአዳም ልጆች ከታሰሩበት የዕዳ ደብዳቤ ነጻ የወጡበት የሰው ልጆች የነጻነት ቀን ነው ብለዋል።
በባሕሪው ፍቅር የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን በፍቅሩ አንድ እንዳደረገ ሁሉ ዛሬም የእርሱን ባሕሪ በመላበስ በፍቅር ልንኖር ይገባል ነው ያሉት አቡነ በርናባስ።
የሰማይና የምድር ፈጣሪ ኾኖ ሳለ በፍጡሩ እጅ የተጠመቀው ዛሬም ነገሥታቱ ዝቅ ብለው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ትህትናን ለማሣየት ነው ያሉት ብጹዕነታቸው በጥምቀቱ የተገኘውን ሰላምና አንድነት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የመለያየት፣ የመጣላላት፣ የመገዳደል አባት ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ነው” ያሉት ብጹዕ አቡነ በርናባስ የሰው ልጅ ከዚህ ተግባር በመለየት አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን በመላበስ በዓሉን ማክበር ይገባል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አሥተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!