
ባሕር ዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጌታን መንገድ አዘጋጁ፥ ይሄድበት ዘንድ ጥርጊውንም አቅኑ፥ ተራራው ዝቅ ይበል፥ ኮረብተውም ሜዳ መኾን አለበት፤ ስጋ የለበሰ ሁሉ ቀና እና ታዛዥ አገልጋይም መኾን አለበት እያለ ሰዎችን ሲያጠምቅ አይሁዶች እና ጸሐፍት ፈሪሳውያን አንተ ማነህ? ምንድነህ? ሲሉ የሚሠራውን መልካም ሥራ በክፉ ይቀይሩበት ዘንድ ወደእሱ መጥተው ጠየቁት።
እሱም ዮሐንስ እንደሚባል ነገራቸው። ሰዎችን በውኃ ያጠምቅ ነበር እና እሱ በውኃ እንደሚያጠምቅ እና ከሱ በኋላም በእሳት እና በመንፈስ የሚያጠምቅ እንደሚመጣ ገለጸላቸው።
ቀና ልብ የነበራቸው ሁሉ ምን እንዲያደርጉ እንደሚወድ ጠየቁት፥ እሱም ማንም ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው እንዲሁም ለተራበው እንዲያካፍል፤ ከሕግ ከተወሰነው በላይ እንዳይጠይቁ እና ትህትናን እና ምግባርን ሁሉ ገንዘብ ያደርጉ ዘንድ አስረዳቸው።
ዮሐንስ ሁሌም እንዲህ ያደርግ ነበር እና በወቅቱ ኢየሱስ 30 ዓመት ሞልቶት ነበር እና ይጠመቅ ዘንድ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረው ወደ ዮርዳኖስ ባሕር ወረደ።
ሕዝቡም እየተጠመቀ ሳለ ኢየሱስ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ በገባ ጊዜ ዮሐንስ ማን እንደኾነ አውቆ የማጥመቅ አቅሙ እንደሌለው ቢገልጽም ይህ ይኾን ዘንድ ግድ ነበር እና ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው።
በዚያም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ተመስሎ በትክሻው ላይ አረፈ፤ ከሰማይም የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተም ደስ ይለኛል ሲል ሦስትነቱን እና አንድነቱን አስተባብሮ ገለጸ።
ይህችም ድንቅ ክስተት በሰው ልጆች ሁሉ እየታሰበች እዚህ ደረሰች። በባሕር ዳር ጽርሐአርያም ደብረሲና በዓታለማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ እና የሐዲሳት መምህር አብርሃም ሞላ እንደነገሩን የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ታቦታትን ይዞ ወንዝ ወርዶ ማክበር የተጀመረው በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ነበር።
ይበልጥ ተጠናክሮ በወንዝ ዳር እንዲከበር የተደረገው ግን በ544 ዓ.ም በአጼ ገብረመስቀል ዘመን እንደኾነ ይገልጻሉ። በተለይም ከያሬድ ዝማሬ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ጥር 11 ታቦታቱ ጠዋት በዝማሬ ወርደው ማታ እንዲገቡ ይደረግ እንደነበር ነግረውናል።
የሐዲሳት መምህሩ እንደነገሩን በቅዱስ ላሊበላ ዘመን ቤተክርስትያናት በተናጠል ያከብሩት የነበረውን የጥምቀት በዓል ወደ አንድ እንዲመጡ እና የየአጥቢያው በጋራ እንዲያከብሩ ሥርዓት መሥራታቸውን ነው ያስረዱን።
የክርስቶስ መጠመቅ ለሕዝብም ለአሕዛብም በመኾኑ በአንድ ላይ እንዲከበር መደረጉ ፍቅርን እና አንድነትን ብሎም ድምቀትን ስለማምጣቱ መምህሩ ይገልጻሉ።
መምህሩ በየጊዜው የነበሩ መሪዎች ይህን እንዳስቀጠሉ እና አጼ ናኦድ በመጽሐፈ እያሱ የአምላካችሁን የቃልኪዳን ታቦታቱን ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁት ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት የሚለውን እያሱ ምዕራፍ 3 ፥ 3 ላይ ያለውን መልዕክት ጠንቅቀው የሚያውቁ ንጉስ ስለነበሩ ይህን ስለመተግበራቸው እና ሕዝቡም ይህን እንዲያደርግ ሥርዓት መሥራታቸውን ነው ያብራሩት።
በአጼ ዘርዐያዕቆብም ታቦታቱ ጥር 10 ወርደው ሳይመለሱ በዛው አድረው ሀገር እየባረኩ በመጡበት ሳይኾን በሌላ መንገድ እንዲመለሱ ስለማድረጋቸውም ነው የሚናገሩት።
ይህም ምሥጢራት እንዳሉት ገልጸዋል። አሁን ላይም የቃልኪዳን ታቦታትን ይዞ ወንዝ ተወርዶ በዓለ ጥምቀቱ መከበር የጀመረውም ከዚህ የተነሳ እንደኾነም አትተዋል።
በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ ታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረዳቸው ምሳሌው ታቦታቱን የያዙት የቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌዎች ሲኾኑ ታቦታቱን የሚያጅቡት ደግሞ ወደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ይመጡ የነበሩ ሰዎች ምሳሌ እንደኾነ ተናግረዋል።
ታቦታቱ በዛው ማደራቸው ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ ተራውን ሲጠብቅ ቆይቶ መጠመቁን ለማጠየቅ እንደኾነም አስገንዝበዋል። በወንዝ ዳር ድንኳን መጣሉ ከዮሐንስ ሊጠመቁ ይሄዱ የነበሩ ሰዎች ድንኳን ተክለው ያድሩ ስለነበር ያን አብነት ተደርጎ ዛሬም ታቦታቱ በድንኳን እንዲያድሩ መደረጉን ነው ያብራሩት።
ዲያብሎስ ከሚያደርስባቸው መከራ የተወሰነ ለማረፍ የእዳ ደብዳቤ አዳም እና ሔዋን እንዲጽፉ ያስደረጋቸው ጠላታቸው የጻፉትን ደብዳቤም አንዱን በዮርዳኖስ ባሕር ሌላውን ደግሞ በሲኦል ደብቆት ስለነበር በዮርዳኖስ የነበረውን የአዳም የእዳ ደብዳቤ በጥምቀቱ ለማጥፋት ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱን የሐዲሳት መምህሩ ነግረውናል።
ጥምቀት ሲከበር የተጣላ ታርቆ እና የተራራቀ ተቀራርቦ ሊኾን እንደሚገባውም መምህሩ አስገንዝበዋል።
የሐዲሳት መምህሩ እሱ ጌታ መምህር ፈጣሪ ኾኖ ሳለ ዝቅ ብሎ በፈጠረው ዮሐንስ መጠመቁ ትህትናን ለመግለጽ ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑ ነው የነገሩን።
ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሲሄድ በታላቅ እና ታናሽ፣ በሃብታም እና በደሃ መካከል ልዩነት እንዳይኖር ለማድረግ ራሱን ዝቅ ስለማድረጉ ነው ያብራሩት።
መምህሩ ሰዎች አባታቸው አንድ አዳም በኋላም አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ተረድተው ከመለያየት እና ከጥላቻ እንዲሁም ከመነቃቀፍ ታቅበው ጥምቀቱን እንዲያከብሩም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!