
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ዓባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ 11 ታቦታት ዓባይ ወንዝ ዳርቻ በሚገኘው ባሕረ ጥምቀት አርፈዋል።
ታቦታቱ በካሕናት፣ ዲያቆናት እና መዘምራን በዝማሬ፤ የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ በእልልታ እና በሆታ ታጅበው ነው ባሕረ ጥምቀቱ ላይ የደረሱት።
ሊቀ ማዕምራን አማረ ጌጡ የመካነ ሰላም ቅድስት አርሴማ አሥተዳዳሪ ናቸው። የከተራ እና የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመጓዝ ትሕትናን ያሳየበትን ለማሰብ የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።
የሰው ልጅ ሁሌም እኔ እበልጣለሁ ከሚል አስተሳሰብ መውጣት ይገባል ያሉት ሊቀ ማዕምራን አማረ ሰውን በክፉ ማሸነፍ አይቻልም ነው ያሉት። “የማሸነፍ ዘዴው ከኢየሱስ ክርስቶስ የምንማረው ትህትና ነው”ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የጥምቀት በዓልን የተለየ የሚያደርገው ሕዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ ወጥቶ ታቦታቱን በዝማሬ ማጀባቸው ነው ብለዋል።
ጥምቀትን ሕዝበ ክርስቲያኑ ዘር እና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ማክበራቸው ሕዝብን ከማቀራረብ ባለፈ የመረዳዳት ባሕልን ያጎለብታል ብለዋል።
ወጣቱ ባሕሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ሥርዓቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ ማክበሩ የሚደገፍ እና ወደ ፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እሴት እንደኾነ ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓልን የውጭ ሀገር ዜጎችም በኢትዮጵያውያን አልባሳት ደምቀው ያከብሩታል ያሉት አቶ አስሜ የሰላም፣ የአንድነት፣ የመቻቻል ተምሳሌት የኾነችው ባሕር ዳር የጥምቀት በዓል ዋና መድመቂያዋ ነው ብለዋል።
በጥምቀት በዓል ከተማዋን በጉልህ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው።
በተጨማሪም ሰላም ከሌለ በዓሉን ማክበር አይቻልም ያሉት አቶ አስሜ ግጭት የሚያስከትለው ጥፋትን ነው ብለዋል። የሕዝቡ ፍላጎት ሰላም ስለሆነ ልዩነትን በውይይት እና ድርድር መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዓሉን ከኦሮሚያ ክልል መጥታ እያከበረች መኾኗን የነገረችን ወጣት ርብቃ “ጥምቀት የአንድነት እና የሰላም ምሳሌ ነው ብላለች። ጥምቀት ሁሉም ያለቀለም እና ዘር ልዩነት የሚከበር እንደኾነም ገልጻለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!