
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አበው የሚመላለሱበት፣ በብፅዕና የሚኖሩበት፣ ምስጢር የሚያሜሰጥሩበት፣ ጥበብ የሚያፈልቁበት፣ ታሪክ የሚያከማቹበት፣ ሃይማኖት የሚያጸኑበት፣ ገዳማት የበዙበት፣ መናንያን የበረከቱበት፣ አማኞች እጅ የሚነሱበት ሐይቅ ከጥንት እስከዛሬ ያረግድላታል፡፡
ሊቃውንቱ በሠርክ በማሕሌት፣ አማኞች በምሥጋና እንደሚያመሠግኗት፣ በማዕልት እና በሌሊት ውዳሴ እንደሚያቀርቡባት ሁሉ ሐይቁም በሠርክ ያረግድላታል፡፡ በማዕበል እየተገፋ ክብርን ይሰጣታል፡፡ በአጸዷ ግርጌ ይመላለስባታል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚጠሩት ታላቁ አፍላግ ግዮን ያጅባታል፡፡
ውኃ በውኃ ላይ የሚያልፍባት፣ ሐይቅ እና አፍላግ ለክብሯ የሚሽቀዳደሙላት፣ አበው በምሥጋና የሚበረቱባት፣ ለውዳሴ የሚጣደፉባት፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጸኑባት፣ ቅዱሳኑ ሥርዓት የሠሩባት፣ ታሪክ የጻፉበት፣ ቃል ኪዳን ያተሙባት፣ ሃይማኖት ያስተማሩባት ቅድስት ናት፡፡ ቅዱሱ በመንፈስ ቅዱስ ገደሟት፡፡ የከበረ ቃል ኪዳንም አተሙባት፡፡ ባሕታውያን ተመላለሱባት፣ ባዕታቸውን በአጸዷ ግርጌ አድርገው ኖሩባት፡፡ ለሀገር ሰላም እና ፍቅር ጸለዩባት፡፡ ዓለምን ንቀው ጸለሉባት፡፡ ደቀመዛሙርቱ ዕውቀትን ይገበዩ ዘንድ ከተሙባት፡፡
ሊቃውንቱም ዕውቀትን እንደ ምንጭ አፈለቁባት፡፡ ጥበብን ከጥበብ ባለቤቱ ተቀብለው መገቡባት፡፡ በእርሷ ፊት ውኃ ውኃን ይሸከማል፡፡ ምስጢራዊው ሐይቅ እና ምስጢራዊው አፍላግ ግዮን ድንቅ ነገርን ያደርጉባታል የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም፡፡ በዚህች ገዳም አያሌ ታሪኮች ሞልተዋል፡፡ ነገሥታቱ እጅ እየነሱ ስጦታ ሰጥተዋታል፡፡ ለክብሯ የተገባውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በአጸዷ በሥርዓት የቆሙት ዛፎች ደስታን ይሰጣሉ፡፡ ገዳማውያኑ ለአገልግሎት ይፋጠናሉ፡፡ አማኞች ለበረከት ይመላለሳሉ፡፡ አዕዋፋት በኀብረ ዝማሬ ያዜማሉ፡፡
ደብረ ማርያም ዓባይ እና ጣና የሚተላለፉባት፣ የተፈጥሮውን ውብ ገጽታ የሚያሳዩባት ጥንታዊት ገዳም ናት፡፡ የጥንቱን ትናገራለች፡፡ የዛሬውን በጥበብ ትጠብቃለች፡፡ ሥርዓትን ታጸናለች፡፡ የነገውን በመንፈስ ቅዱስ ታሳምራለች፡፡
ስለ ጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም የተጻፈው ታሪክ ገደሟ በአጼ ይኩኑ አምላክ ዘመነ መንግሥት እንደተመሠረተች ከትቧል፡፡ የመሠረቷት ደግሞ አቡነ ታዴዎስ የተባሉ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ እኒህ ጻድቅ ሰው ትውልዳቸው ሸዋ ጽላልሽ በተባለ ሥፍራ ነው፡፡ አባታቸው ቀሲስ ሮማንዮስ እናታቸው ደግሞ ማርታ ይባላሉ፡፡ አባታቸው የጻዲቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት እንደኾኑ ይነገራል፡፡ እኒህ ካህን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚበረቱ ነበሩ፡፡ እናታቸውም ጸጋን የታደሉ፡፡ እኒያ ደጋግ ሰዎች በመልካም ልብ መልካም ፍሬ ተሰጣቸው፡፡ አቡነ ታዴዎስን የመሰሉ ልጅ ተቸራቸው፡፡
አቡነ ታዴዎስ በእናታቸው ማሕጸን ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር ያልተለያቸው ነበሩ ይባላል፡፡ በረከት የበዛላቸው፣ አምላክ የወደዳቸው ናቸው፡፡ በልጅነት ዘመናቸው እንደ ሕጻናት አይዘፍኑም፡፡ አይጫወቱም፡፡ በዋዛ እና በፈዛዛ የምታልፍ ጊዜ አልነበረቻቸውም ይላል ታሪካቸው፡፡ ይልቅስ በእናታቸው ጀርባ ኾነው ወደ ቤተክርስቲያን በሄዱ ጊዜ ካህናት አምላካቸውን ሲያመሠግኑ ሲያዩ እጃቸውን አውጥተው ያጨበጭቡ ነበር እንጂ፡፡ ይህን ያዩ ሁሉ ይደነቁባቸው፣ ይገረሙባቸው ነበር፡፡
እኒህ አባት በጥበብ እና በሞገስ አደጉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ከአበው እግር ሥር ተቀምጠው ተማሩ፡፡ በጸሎት እና በተጋድሎም ጸኑ፡፡ ዓለምን ናቁ፡፡ በተጋድሎ በረቱ፡፡ መገኛቸው ገዳማት እና አድባራት ኾነ፡፡ ለአቅመ አዳም በደረሱ ጊዜ ወላጆቻቸው አግብተው ይኖሩ ዘንድ ፈለጉ፡፡ እርሳቸው ግን ለምንኩስና የተመረጡ ነበሩ እና ከጋብቻ ራቁ፡፡ አስኬማ ደፍተው፣ በትረ ሙሴ ጨብጠው፣ ስጋቸውን በጾም እና በጸሎት እያደከሙ በባዕት መኖርን መረጡ እንጂ፡፡
ዓመታት አለፉ፡፡ አቡነ ታዴዎስ በስማቸው ገዳም ይገድሙ ዘንድ ታዘዙ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም እየተመሩ ወደ ታላቁ ሐይቅ ወደ ጣና ገሰገሱ፡፡ በጣና ሐይቅም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ታዝዘዋልና፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የታዘዙትንም ፈጸሙ፡፡ ታላቋን ገዳም ደብረ ማርያምን አነጹ፡፡ በገዳሟም ሥርዓት ሠሩባት፡፡ ቃል ኪዳን አተሙባት፡፡ የእርሳቸው ቃል ኪዳንም ዘመናት አልፎ ዛሬም እንደጸና ይገኛል፡፡
ገዳሟ በመንፈስ ቅዱስ ከኢየሩሳሌም በመጣ ድንጋይ እና ጭቃ እንደተሠራች በጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም ታሪክ ላይ ተመዝግቧል፡፡ በገዳሟ ያለምክንያት እና ያለ ምልክት የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ሁሉም በጥበብ እና በመንፈስ ቅዱስ ተገነባ እንጂ፡፡ በቅኔ ማሕሌቱ ዙሪያውን በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ አሥራ ሁለት አምዶች ይገኙበታል፡፡ ወደ መቅደስ መግቢያው የሚያመሩ ካህናት የሚመላለሱባቸው በአራቱ ወንጌላውያን በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስ እና በዮሐንስ የተሰየሙ መተላለፊያዎች አሉ፡፡ ጣራው እና ሕንጻው በመንፈስ ቅዱስ የታነጸ ነው፡፡ በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌ የኾኑ ሃያ አራት አምዶች ይገኛሉ፡፡
የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ ቀሲስ መሐባው አለበል ይህች ገዳም ቅዱሳን የኖሩባት፣ የሚኖሩባት ጥንታዊት ናት ይላሉ፡፡ የጥንት ታሪክ ያለባት፡፡
ድንቅ ናትም ይሏታል፡፡ መሠራቿ አቡነ ታዴዎስ ባስቀመጡት ሥርዓት መሠረት ዛሬም ትተዳደራለች፡፡ የአበው ቃል ኪዳን ይከበርባታል፡፡ ትውፊትም ይጸናባታል፡፡
በደሴቷ ጅራፍ አይጮህባትም፣ በሬም አይጠመድባትም፡፡ ይህ ይኾን ዘንድ አልተፈቀደምና፡፡ ይልቅስ በዚያች ደሴት የሚኖሩ ሁሉ እየቆፈሩ ዘር ይዘራሉ፡፡ ፍሬም ያገኛሉ እንጂ፡፡ በቅድስቷ ሥፍራ የአበው ቃል ይጠበቃልም ይከበራልም፡፡ ይህም ሥርዓት ተጠብቆ ለልጅ ልጅ ይተላለፋል፡፡ ይህች ሥፍራ ቅዱሳን አባቶች ይገኙባታል፡፡ የማይታዩት ስውራኑ አባቶች በሌሊት ኪዳን ያደርሱባታል፤ ማሕሌት ይቆሙባታል፡፡ ስብሐተ እግዚአብሔር ያበዙባታል ነው የሚሉት ቀሲስ፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ ብርቅና ድንቅ የኾኑ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ሞልተዋል፡፡ ጥንታውያን መጻሕፍት፣ መስቀሎች፣ የነገሥታት ሥጦታዎች፣ ጥንታውያን ሥዕሎች ይገኛሉ፡፡ በዚህች ድንቅ ገዳም የመሠረቷት አባ ታዴዎስ በአምላካቸው ኀይል ሙት ያስነሱበት መስቀል እና መቋሚያቸውም አሉ፡፡ የነገሥታት ዘውዳቸው፣ ካባቸው፣ የክብር ሥጦታዎቻቸውም በዚህች ጥንታዊት ገዳም በክብር ተቀምጠዋል፡፡ ነገሥታቱ እጅ እየነሱ፣ ጸሎት እያደረሱ መብዓ አቅርበውባታል፡፡ ለስማቸው መነሻ፣ ለታሪካቸው ማስታወሻ ሥጦታ አስቀምጠውበታልና የመጣ የሄደው ሁሉ የነገሥታቱ ታሪክ ይሰማል፡፡ ይማራል፡፡
በዚህች ገዳም በዓለ ጥምቀት ይለያል፡፡ ግሩም ድንቅ ነውና፡፡ ታቦቷ ከመንበሯ ወጥታ ወደ ሐይቅ ትወርዳለች፡፡ በሐይቅም ትመሠገናለች፡፡ በወንዝም ትታጀባለች፡፡ በሐይቅ ላይም ትመላለሳለች፡፡ በአፍላግ ላይም ታጌጣለችና፡፡ አማኞች በታንኳ ኾነው ለክብሯ እጅ ይነሱላታል፡፡ ሐይቁን እያማቱ ምሥጋና እና ውዳሴ ያቀርቡላታል፡፡ ስለ ምን ቢሉ እርሷ እናታቸው፣ መመኪያቸው ናትና፡፡ ቀደም ሲል በታንኳ ብቻ ትታጀብ ነበር አሁን ግን ዘመናዊ ጀልባዎችም አሉና እጀባው በሁለቱም ነው ይላሉ ቀሲስ፡፡
ታቦቷ በታላቅ ክብር በጣና ሐይቅ ላይ ትታያለች፡፡ ወጣቶች በደስታ እና በምሥጋና ታንኳ እየቀዘፉ ለክብሯ ይፋጠናሉ፡፡ ካህናቱ ታቦቷን ይዘው ይዘምራሉ፡፡ ታቦቷም ሐይቋን ትባርካለች፡፡ ትቀድሳለች፡፡ አማኞች እልል ይላሉ፡፡ ከዓመት ዓመት ታደርሳቸው ዘንድ ስለትን ያገባሉ፡፡ በጥንቱ ሥርዓት መሠረት ከመንበሯ ወጥታ ወደ ሐይቅ እየወረደች፡፡ በሐይቅም እየተመላለሰች፤ ሐይቁንም እየባረከች ትኖራለች፡፡
ጥምቀት በደረሰ ጊዜ ደብረ ማርያም አብዝታ ትናፈቃለች። አማኞች በታንኳ እና በጀልባ ወደ እርሷ ይጓዛሉ፡፡ እርሷንም አጅበው ወደ ሐይቅ ይወርዳሉ፡፡ በዙሪያዋ ይመላለሳሉ፡፡ በድንቅ ሥርዓትም ይመሰጣሉ፡፡ ሂዱና ተመልከቷት፡፡ ድንቁን ነገር ታዩበታላችሁ፡፡ ውበትንም ታደንቃላችሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!