
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ጥምቀት የሃይማኖቱ ተከታዮች እና ዓለምአቀፍ ቱሪስቶች በናፍቆት የሚጠብቁት ተወዳጅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ፈጣሪ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር እና ትሕትና ያሳየበት ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የሚወራ ሳይኾን የሚኖሩት ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ያደረገው በሰዎች መካከል ፍቅር እንዲኖር ከማሰብ እንደኾም ገልጸዋል።
ሀገሩን የሚወድ ሁሉ በመከባበር፣ በመተሳሰብ እና አብሮነትን በመተግበር የክርስቶስን አርዓያ መከተል ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጥላቻን በፍቅር፣ ግጭትን በይቅርታ በመለወጥ የጥምቀት በዓልን አብነት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሰው ከፈጣሪው ይቅርታ እና ምህረት ለማግኘት ፍቅርን በልቡ ውስጥ መትከል ይገባዋል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። የሃይማኖቱ አስተምህሮም የሚያስተምረው ይቅርታ እና ፍቅርን ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
አሁን የሚታየው ጥላቻ፣ ዘረኝነት እና መገፋፋት ክርስቶስ ካስተማረው በተቃርኖ ስለሚታይ ወደ ክርስቶስ ፍቅር መመለስ እንደሚገባም አብራርተዋል። የአማራ ሕዝብ ችግር የሚፈታውም ወንድም ከወንድሙ በመገዳደል ሳይኾን በምክክር በይቅርታ እና በእርቅ በመወያየት መኾን እንዳለበት አሳስበዋል።
የጥምቀት በዓል ከየዓለሙ ዳርቻ የውጭ ዜጎች ሊጎበኙት የሚመጡበት በዓል እንደኾነም ነው የተናገሩት። ይህን ትልቅ በዓል የአማራ ክልል እና የባሕር ዳር ነዋሪ በእንግዳ አክባሪነት ስለሚያስተናግድ ምሥጋና ይገባዋል ነው ያሉት። ይህ በዓልም ሳይበረዝ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የአማራ ክልል ሰላም ችግር ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ እየተሻሻለ በመኾኑ እንዲህ ዓይነት በዓላትን በተሻለ ሰላም እያከበረ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
የሕዝቡ ታጋሽነት እና ሰላም ፈላጊነት እንዲሁም የጸጥታ ኀይሎች መስዋዕትነት ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመጣ እንዳስቻለውም ጠቁመዋል።
የጥምቀት በዓል ከሃይማኖቱ ተቋማት እና መሪዎች ጋር በመመካከር የበዓሉ አስኳል እንዲኾን ጠንክረው እንደሚሠሩም አስረድተዋል።
የከተማው ወጣቶችም ለሰላም እና ለበዓሉ መከበር ላደረጉት አስተዋጽኦ አመሥግነዋል። የከተማው ነዋሪዎች ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባቸውም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!