“በኅብረትና በአንድነት የምናክብረው የከተራና የጥምቀት በዓል፣ ትህትናን አስቀድመን፣ ደግነትን ተላብሰን ለሰላምና ለፍቅር የምንዘምርበት በዓል ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

25

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል ያስተላለፉት መልእክት።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እጅግ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ትህትናን የምንማርበት፣ መዳንን እና ተስፋን የምንሰንቅበት ከሃይማኖታዊ ትውፊት እስከ ባሕላዊ ይዘት ፈርጀ ብዙ ትርጓሜ ፤ መልከብዙ ትእይንት ያለው በዓል ነው።

ጥምቀት ፈጣሪ በፍጡር፣ አምላክ በሰው፣ ጌታ በአገልጋዩ የተጠመቀበት እለት ነው። በሥርአተ ጥምቀቱ አምላክ ከነበረበት ከፍታ ወርዶ ከሰው የተስተካከለበት፣ ከቆመበት የጌትነት ስፍራ ዝቅ ብሎ ትኅትናን ያሳየበት፣ ትእቢትን ሽሮ ለሰው ልጆች ትኅትናን ያስተማረበት ሥርዓት ነው።

በመላው የሀገራችን አካባቢዎች በኅብረትና በአንድነት የምናክብረው፣ በአብሮነታችን የምንደምቅበት ይህ በዓል ትህትናን አስቀድመን፣ ደግነትን ተላብሰን ለሰላምና ለፍቅር የምንዘምርበት በዓል ነው።

የከተራ እና ጥምቀት በዓላት ከመንፈሳዊ ገጽታዎቻቸው ባሻገር ያሏቸው ባህላዊና ትዕይንታዊ ሁነቶች የሚሊዮኖችን ቀልብ የሚስቡ በመሆናቸው እነዚህን ለመታደም በርካቶች ባሕር አቋርጠው ወደ ክልላችን እና ሀገራችን ይመጣሉ።

በመሆኑም የበዓላቱን ሁነቶች ለመልካም ገጽታ ግንባታ በመጠቀም፣ አከባበር ሂደቱም ለአብሮነታችንና ለመደጋገፋችን ወረት ተጨማሪ እሴት የምናጎለብትበት እንዲሆን ማድረግ ይገባናል።

በድጋሜ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል አደረሳችሁ። መልካም የከተራ እና የጥምቀት በዓል እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ።

መልካም በዓል።

Previous articleየቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊ ካሳ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ጎንደር ገቡ።
Next articleበሁመራ ከተማ ታቦታቱ ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ተከዜ ወንዝ ጥምቀተ ባሕር እየወረዱ ነው።