“ጥምቀት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው የአደባባይ የወል በዓል ነው” የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት

25

ባሕርዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል።

በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱ ጥምቀት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው የአደባባይ የወል በዓል ነው፣ በዓሉ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሚታይ ለዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተበረከተ ሀብታችን ነው ብሏል።

የበዓሉ መሠረት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሃይማኖታዊ መሠረቱን እንደያዘ ባሕላዊ እሴት እንዲኖረዉ ጭምር አድርገውታል ነው ያለው። በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ባሻገር መላው ሕዝብ የሚታደምበት የዓደባባይ የወል በዓል ተደርጓል ብሏል። ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ ያበረከተችው የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡም ለዚህ ማሳያ ነው መኾኑን ነው ያመላከተው።

የጥምቀት በዓል ከሌሎች የሃይማኖታዊ በዓላት ለየት የሚያደርገዉ በሃይማኖት ተቋማት ቅጥረ ግቢ፣ በቤት ውስጥ ብቻ የሚከወን አለመኾኑና ደስታን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ማጋራቱ ነው ብሏል። በሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ አልባሳት ያጌጡ ምዕመናንና ታዳሚዎች በጋራ የሚያከብሩት ድንቅ በዓል መኾኑንም ገልጿል።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት፣ መዝሙሮች እና ባሕላዊ ጭፈራዎች ባሻገር የገና ጨዋታ እና የፈረስ ግልቢያ መሰል ኹነቶች የሚያደምቁት ነው፡፡ ይህንን ትውፊቱን የጠበቀ በዓል ጎብኝዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመታደም ዐቅደዉ ይመጣሉ ነው ያለው። የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ፣ የሕዝቧን አብሮነት እና እንግዳ ተቀባይነት ተመልክተውበትም ይመለሳሉ ብሏል።

በዚህ በዓል ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እና ሚና ልቆ እንደሚታይም አመላክቷል። ታቦታቱን ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ በዝማሬ እና ጭፈራ ያጅባሉ፤ የታቦታቱን መንገድ ይጠርጋሉ፤ ምንጣፎችን ያነጥፋሉ፤ ይሸከማሉ ነው ያለው፡፡ ይህ ጠንካራ ማኅበራዊ እሴት እየዳበረ መምጣቱን ገልጿል።

የጥምቀትንም በዓል ስናከብር ጥንታዊ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ትውፊቱን ጠብቀን፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናን፣ ወጣቶች እና መላዉ ሕዝባችን የነበረ ሚናችንን እየተወጣን ሊኾን ይገባል ብሏል በመልዕክቱ። በዓሉ ደስታን የምንጋራበት የዐደባባይ በዓል ነውና ደስታችንን እየተጋራን ልናከብረው ይገባል ነው ያለው።

ለመላዉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እና ለበዓሉ ታዳሚዎች በሙሉ እንኳን ለከተራ፣ ለጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ ብሏል በመልዕክቱ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰቆጣ ከተማ የከተራ በዓል ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ እየወረዱ ነው።
Next articleየቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊ ካሳ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ጎንደር ገቡ።