ጌጥ እና ውበት በጥምቀት

36

ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓደባባይ ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡

‹ጥምቀት› ማለት በውኃ ውስጥ መጠመቅ፣ መጥለቅ፣ መንጻት ማለት እንደኾነ ሃይማኖታዊ አስተምሮው ያስረዳል፡፡ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ ፤ ጥምቀትን ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ሃይማታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱ ከሌሎች የተለየ ነው ይላሉ፡፡

ጥምቀት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ከመንጻት ጋር ስለሚያያዝ ሰው ጸዓዳ ኾኖ፣ ለዓይን የሚስቡ አልባሳትን በመልበስ፣ እንደየ አካባቢው የተለያዩ ማስጌጫዎችን በመጠቀም አምሮ እና ደምቆ ታቦታትን ለማጀብ ሁሉም የሚታደምበት ቀን ነው ፡፡

በጥምቀት እንደየ አካባቢው የተለያየ ዓይነት አለባበስ ቢኖርም ሁሉም እንደ ባሕሉ እና ወጉ “ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንደሚባለው ጸዓዳ የኾነ የክት ልብሱን በመልበስ ፣ የተለያዩ የጸጉር አሠራሮችን፣ ባሕላዊ መዋቢያዎችን እና ጌጣጌጦችን ተጠቅሞ አምሮ እና ደምቆ መውጣት የተለመደ ነው፡፡

ልጃገረዶቹ ሹርባ፣ ጋሜ እና ቁንጮ በመሠራት ጸጉራቸውን አስጊጠው እግር እና እጆቻቸውን በእንሶስላ አስውበው፣ አልቦ እና ድሪያቸውን አጥልቀዉ፣ ታቦታትን አጅበው “እሰይ ስለቴ ሰመረ የልቤን እንዲያደርስ ነግሬው ነበረ” በማለት ታቦታቱን በጭብጨባ እና በእልልታ ያደምቁታል፡፡

ወይዘሮ ነበሬ አበራ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ ድሮ ገጠር እያለሁ ያሳለፍኳቸውን የጥምቀት በዓላት መቸም አልረሳቸውም ይላሉ። ያኔ ጥምቀት ልዩ ነበር ነው የሚሉት። በጥምቀት አምሮ እና ደምቆ ለመውጣት ቀደም ብለን ነበር የምንዘጋጀው ይላሉ።

እንሶስላ ፣ልብስ ይገዛልናል፣ ዓሳ ቅርጽ የሚባል ሹሩባ እንሠራለን፣ ጋሜው፣ ቁንጮው፤ ብቻ ለመዋብ ሁሉም እንደየ ፍላጎቱ ቀድሞ ይዘጋጃል ይላሉ የቀደመውን ሲያስታውሱ።

ስለ ትዝታቸው ሲነግሩን በተለይ በጥምቀት ዋዜማ የተገዛልንን እንሶስላ ከየቤታችን እናወጣ እና ከአንዳችን ቤት ለመሞቅ ይፋቃል፣ በደንብ ይታጠባል፣ ይሰለሰልና ሰፋ ባለ ሸክላ ድስት ተጥዶ መሞቅ እንጀምራለን።

የጥምቀት ዕለት በጠዋት ተነስተን የመጀመሪያ ሥራችን የማን እጅ የበለጠ አማረ የሚለውን ማየት ነበር። ይህ ደግሞ ደስ የሚል የመወዳደር ስሜት ይሰጥ ነበር ነው ያሉት።

በተለይ ልጃገረዶቹ ኩሉን ተኩለው፣ በአርቲ እና በስንቡል የታሸ ልዩ ማዕዛ ያለው ቅቤ ተወዝተው፣ የእጅ አምባሩን እና ድኮቱን አጥልቀው፣ የጆሮ ጌጣቸውን አሳምረው ፣ ሻሻቸውን ሸብ አድርገው የሚያምር አዲስ ጃንጥላቸውን በመያዝ እልል እያሉ መዋሉ አይረሴ ድምቀት አለው ።

ጎበዛዝቱ ደግሞ ያማረ ቁምጣቸውን በቁልፍ ካጌጠ አላባሽ ኮት ጋር ግጥም አድርገው ለብሰው፤ ሽመላቸውን ሽቅብ ከፍ በማድረግ እንደየ አካባቢያቸው “ሆሆ” እያሉ ታቦታትን አጅበው ሲሸኙ ሲታይ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል ፡፡

የተለያዩ ባሕላዊ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ ሕብር የኾኑ መድመቂያ እና ጌጣጌጦችም ይታያሉ፡፡ ብቻ ጥምቀት ልዩ ድምቀት ነው። ለጥምቀት የሚቆጠብ ፣ የሚሳሳለት የለም።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተገነቡ የውኃ ፕሮጀክቶችን መረቁ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ በዓባይ ወንዝ ዳርቻ የሚያድሩ ታቦታት በድምቀት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ እየወረዱ ነው።