
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአርጡማ ፉርሲ እና በደዋ ጨፋ ወረዳዎች የተገነቡ ሦስት የውኃ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አሥተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ አሊ እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ጨፋ በከርሰ ምድር እና በገፀ ምድር ውኃ የታደለ አካባቢ ነው። አማራ ክልል የውኃ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን መታዘባቸውንም ገልጸዋል።
አንዳንድ ቦታዎች ፕሮጀክቶች ቢጀመሩም የሚከታተላቸው ግን አልነበረም፤ የክልሉ ቢሮ አመራሮች እነዚህን ፕሮጀክቶች በአካል እየተገኙ በመከታተል እንዲጠናቀቁ አስችለዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የአካባቢውን የውኃ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ዞኑን ሲመለከቱ የሕዝቡ አንዱ ችግር የውኃ አቅርቦት መኾኑን ተገንዝበው እንደነበር ገልጸዋል። በሁለት ዓመት ውስጥ አሁን የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ዛሬ በማስመረቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉንም ገልጸዋል።
ተቋማቸውን በማጠንከር የውኃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ዛሬ የተመረቁት ፕሮጀክቶች ያቀድነውን ጀምረን መተው ሳይሆን መፈፀም የምንችል መኾናችንን ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ እንዲጠናቀቁ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል። ማኅበረሰቡም የተሠራለትን ፕሮጀክት በመጠበቅ ኀላፊነቱን እንደሚወጣም አሳስበዋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የውኃ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን የሕዝቡን ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የውኃ ችግር እንደቀረፈ እና ለውኃ ፍለጋ የሚባክነውን ብዙ ድካም እንደቀነሰ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን