
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለከተራ እና ጥምቀት በዓል አደረሳችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል።
የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በየዓመቱ በደማቅ አከባበር የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው። ሀገራችን በዩኔስኮ በቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ብሔራዊ ቅርሶች መካከል አንዱ የኾነው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ መከበር ከጀመረ ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል።
ሕዝበ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተለያዩ አልባሳት እና ጌጣጌጦች አጊጠው፣ አሸብርቀው እና ደምቀው የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመፈፀም ታቦታቱን በእልልታ እና ጭብጨባ እያጀቡ የከተራ እና የጥምቀት በዓልን በደስታ እና በፍቅር ያሳልፉታል።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ አምልኮተ ሥርዓቱ ባለፈ ለማኅበራዊ ትስስር እና ለአብሮነታችን መጠናከር፣ ለገፅታ ግንባታ እና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ያለው አበርክቶ እጅግ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም የጥምቀት በዓልን ስናከብር ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፋ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚ ልማት የሚያስገኘውን አበርክቶ በመገንዘብ እና ይህንኑ በማጠናከር ሊኾን ይገባል።
የጥምቀት በዓል ፍቅር፣ ሰላም እና ትህትና የተገለጠበት እንደ መኾኑ የከተራ እና የጥምቀት በዓልን ስናከበር ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በጠበቀ፣ ማኅበራዊ ትስስራችንን እና አብሮነታችንን በሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን፣ በፍቅር፣ በሰላም፣ ለተቸገሩ ወገኖች ካለን በማካፈል፣ በመተሳሰብ ስሜትና ተግባራት ሊኾን ይገባል።
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሣችሁ ! አደረሰን!
መልካም በዓል!
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት