
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ኢትዮጵያ በርካታ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት አሏት። በዓላቱም በየዓመቱ በድምቀት ይከበራሉ። አንዳንዶቹን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲቸራቸው እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) እንዲመዘገቡ ማድረግ ተችሏል።
በኢትዮጵያ በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው። ታኅሣሥ 01/2012 ዓ.ም ተመዝግቧል። በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ የበዓሉ ታዳሚ ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ የዓለምን ሕዝብ ቀልብ እንዲስብ አድርጓል ብለዋል።
ምዕመናኑ በዓሉን በሆታ እና ጭብጨባ፣ በእልልታ እና እጀባ ኀብር ፈጥረው ማክበራቸው ጎብኝዎችን አጃኢብ! የሚያሰኛቸው ክዋኔ መኾኑን ባለሙያው ተናግረዋል።
በተለይ ወጣቱ የበዓሉን ዝማሬ በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከናወን እና በመጤ ባሕል እንዳይበረዝ የሚደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነውም ይላሉ።
የነገ ሀገር ተረካቢ የኾነው ወጣቱ አካባቢን ከማስዋብ ጀምሮ በየከተማው ለሚገቡ እንግዶች የሚያደርጉት ኢትዮጵያዊ የኾነ አቀባበል እና መስተንግዶ ልዩ ነው።
ይህ ወጣቱ ለበዓሉ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋሪነትም በግልጽ ያሳያል። ለበዓሉ ክብር በመስጠትም የምንጣፍ ማንጠፍ ሥነ ሥርዓት ይበል ያሰኛል ነው ያሉት ባለሙያው።
የጥምቀት ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም የየራሱን ኀላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!