የጥምቀትን በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

19

ሰቆጣ፡ ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር የወጣቶቹ ሚና የጎላ ነው። የሰቆጣ ከተማ ወጣቶችም የጥምቀት በዓል ከመድረሱ በፊት ከተማውን የማስዋብ እና የታቦታቱን መንገድ የመጥረግ ሥራ ሢሠሩ ሰንብተዋል።

ወጣት ታደሰ ዘነበ የመጋቤ ፍሬዎች ማኅበር ሠብሣቢ ነው። ከሰሞኑ የሰቆጣ ከተማን ውበት ለመመለስ ቆሻሻዎችን በማቃጠል እና መንድ የመጥረግ ሥራ ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጿል።

በከተራ ቀንም ታቦታቱ የሚጓዙበትን ድንኳን የመዘርጋት እና የማጽዳት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹልን። ከተማውን በማስዋብ ሥራ ተሰማርታ አሚኮ ያገኛት ወጣት የትምወርቅ መላሽ ” በሰቆጣ ከተማ ያሉ በጎ አድራጊ ወጣቶች የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ ባለፈ የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ከጸጥታ አካሉ ጋር በቅንጅት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጻለች።

ወጣቱ ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን ጸጥታውን ይቆጣጠራል። መላሽ የተስፈኞቹ ማኅበርም የታቦታቱን መንገድ ከማስተካከል ባለፈ የአቅመ ደካማ ሰዎችን አልባሳት በማጠብ በዓሉን ጸድተው እንዲውሉ ማድረጋቸውንም ገልጻለች።

በሰቆጣ ከተማ ከስድስት በላይ የወጣት ማኅበራት እና በጎ አድራጊ ድርጅቶች የተውጣጡ ከ650 በላይ ወጣቶች ሳምንቱን ከተማዋን በማጽዳት እና የተበላሹ መንገዶችን በመጠገን በኩል ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸውን የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ሙሉቀን ታድጎ ገልጸዋል።

ከከተራ በዓሉ ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ ወጣቱ የተሰጠውን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ቁርጠኛ ነው ያሉት ወጣት ሙሉቀን በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሌት ተቀን ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እጅ እና ጓንት ኾነው እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አባተ የጸጥታ መዋቅሩ ከወጣቶች እና ከማኅበራት ጋር የጋራ በማድረግ በተደራጀ እና በተቀናጀ መንገድ የማኅበረሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

የሰቆጣ ወጣት በዋግ ኽምራ ላለው አንጻራዊ ሰላም መኖር ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ መኾኑን ያስታወሱት ምክትል ኢንስፔክተሩ ሰላሙን የሚያውኩ አካላትን ነቅሶ በማውጣት እንደተለመደው ከወጣቱ ጋር ብሎም ከሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ጋር በንቃት ይሠራል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡም የአካቢውን ሰላም የሚያውኩ አካላትን ለይቶ በማውጣት ለጸጥታ አካላቱ እና ሰላም ለሚያስከብሩ ወጣቶች ጥቆማ በመስጠት በኩል የተለመደ ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በዓሉ የሰላም እና የፍቅር በዓል እንዲኾን ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አባተ ተመኝተዋል ።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዮርዳኖስ አምሳያ ኢራንቡቲ!
Next articleጥምቀት በዚህ ትውልድ!