
ደብረ ብርሃን፡ ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሽዋዋ ኢራንቡቲ ስትነሳ አብሯት የሚታወሰው እንደ ጎንደር ሁሉ የጥምቀቷ ሁነት ነው። 44 ታቦታትን በአንድ ስፍራ የምታወርደው የምንጃር ሸንኮራዋ ኢራንቡቲ የጥምቀተ ባሕሯ የተለየ ገጽታ ያለው ነው።
በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ “በአምሳለ ዮርዳኖስ” የጥምቀት በዓልን ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የኢራምቡቲን ልዩ ገጽታ ለመግለጥ በልዩ ሁኔታ ሲዘጋጅ ቆይቷል።
የመምሪያው ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው ኢራንቡቲን ለመግለጥ የጥምቀተ ባህሩን ቦታ የማደስ እና የማስተካከል ሥራ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል። የኢራንቡቲ ጥምቀተ ባሕር 44 ታቦታት በአንድ ላይ የሚሠባሠቡበት በመኾኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ነው የነገሩን፡፡
በ14ኛው መቶ ከፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከ1394 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ በአካባቢው ሲከበር ቆይቷልም ብለዋል። ታቦታቱ የሚያድሩበት የሸንኮራ ወንዝ በአምሳለ ዮርዳኖስ የተፈጠረ ነው ያሉት ኀላፊዋ ታቦታቱ ወደዛው እንደሚወርዱ ጠቁመዋል፡፡
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራንቡቲ ጥምቀተ ባህር ጥምቀትን ማክበር በብዙ መንገድ ለየት ይላል የሚሉት ኀላፊዋ ወንዙን ከሚለዩት አቀማመጦች መካከል ወንዙ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀበት የዮርዳኖስ ወንዝ ጋር የሚመሳሰል መኾኑ አንደኛው ነው ይላሉ፡፡
ከላይ መነሻው አንድ ኾኖ መሐል ላይ ለሁለት ተከፍሎ ዝቅ ብሎ መገናኘቱ አምሳለ ዮርዳኖስ አሰኝቶታል ብለዋል፡፡ ተፈጥሯአዊ የኾነው ወንዙ የፍሰቱም አቅጣጫ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አድርጎ ከመነሻው ጀምሮ ባለው ተፋሰስ የ44ቱም ታቦታት ጸበል መኖሩ ለየት የሚያደርገው ሁለተኛው ዕውነታ እንደኾነም ነግረውናል፡፡
ከ44ቱ ታቦታት ውስጥ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጽላት አብሮ በጥምቀተ ባህሩ ማደሩ ሌላኛው የዚህ ድንቅ ስፍራ የድምቀቱ ማሳያ ተደርጎም የሚወሰድ ነው፡፡
በዓሉ ከመንፈሳዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ በአካባቢው ባሕላዊ ጭፈራ ይደምቃል። የአካባቢው ወግ እና ባሕልም ጎልቶ የሚታይበት ነው።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!