
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው።
የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ የበርካታ ቱሪስቶች ስበት እየኾነ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ጉልህ ነው። የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የላሊበላ ከተማ ተጠቃሽ ናት።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ልክ እንደ ልደት ሁሉ የጥምቀት በዓልም በልዩ ድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል። የላሊበላ ነዋሪዎች ለልደት በዓል ተሰናድተው፣ በዓሉን በድምቀት እና በሰላም አክብረው እንግዶቻቸውን ሸኝተዋል፤ የጥምቀት በዓል ደግሞ ከልደት ባልተናነሰ መልኩ ለማክበር ዝግጅቶች ተደርገዋል ነው ያሉት ዲያቆን አዲሴ።
የጥምቀት በዓል በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ቢኾንም በላሊበላ ደግሞ ልዩ መልክ ይዞ ይከበራል። በልደት በዓል አስደናቂ ወረብ የተካኑት የላሊበላ ቀሳውስት ይህንኑ ልዩ እና በሌሎች አካባቢዎች ታይቶ የማይታወቅ ወረብ በጥምቀት በዓል ላይም ያቀርባሉ። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት በተለይ ባሕላዊ አለባበሳቸው፣ ዜማቸው፣ ወረቡ እና ሁሉም አይነት የጥምቀት ኹነቶች ልዩ እና የትም ቦታ ቢኬድ ሊገኙ የማይችሉ፣ የቱሪስቶችንም ቀልብ የሚስቡ ናቸው ብለዋል። እነዚህ ሁነቶች ተደማምረው ጥምቀትን በላሊበላ ልዩ እንደሚያደርገውም የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ነግረውናል።
ጥምቀት በላሊበላ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ተገኝተው ይታደማሉ። የጥር ወር በላሊበላ ከፍተኛ የቱሪስት ፍስሰት የሚታይበት ነው፣ ይህም ከበዓሉ ድምቀት በተጨማሪ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለሀገርም ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ነው ብለዋል ዲያቆን አዲሴ።
ላሊበላ የቱሪስት ከተማ ነች፤ ልደትንም ጥምቀትንም በድምቀት ታከብራለች፣ የበለጠ ጎልቶ የሚታወቀው ግን ልደት ነው ብለዋል። ይሁን እንጅ ጥምቀትም ከልደት እኩል ደምቆ የሚከበር፣ የቱሪስቶችን ቀልብም የሚስብ የታሪካዊቷ ከተማ ሁነት መኾኑ መታወቅ አለበት ብለዋል።
ጥምቀት በላሊበላ ያለውን መልክ እና ድምቀት ለዓለም በማስተዋወቅ የልደትን ያህል ጎብኝዎች እንዲታደሙበት ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገልጸዋል። ለልደት በዓል ወደቦታው ያቀኑ ጎብኝዎች ቆይታቸውን እስከ ጥምቀት በዓል በማራዘም በጥምቀትም እንዲታደሙ የሚያስችል ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
ጥምቀት በላሊበላ በድምቀቱ ልክ በቱሪስቶች እንዲጎበኝ የሚያስችል የማስተዋወቅ ሥራ ውስንነቶች እንዳሉበት ኀላፊው ተናግረዋል። ይህንን የማስተዋወቅ ሥራ ከመንግሥት በተጨማሪ ማኅበረሰቡም ጭምር ወስዶ ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና የሕዝብ ነው መጭው የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲውል ማንኛውም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ሲሉም አሳስበዋል ዲያቆን አዲሴ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!