“ጥምቀት አንድነት የሚጸናበት፣ ፍቅር የሚጎለብትበት”

31

ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች ቢተዋወቁም ባይተዋወቁም የጥምቀትን በዓል በጋራ ኾነው ጥዑመ ዜማ እያንቆረቆሩ ያከብሩታል፡፡

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ሳይገድባቸው በአንድ ባሕረ ጥምቀት ተሰባስበው በአንድነት፣ በዝማሬ፣ በዜማ ያከብሩታል። ሰዎች በጥምቀት በዓል ይደማመጣሉ፤ ይከባበራሉ፤ ይተሳሰባሉም።

አበው “ነገርን ከሥሩ፤ ውኃን ከጥሩ” እንዲሉ በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ያላት ሀገር ናት ይላሉ።

ከእነዚህ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ጥምቀት አንደኛው ነው። ጥምቀት በዓሉም ኀብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚስተዋልባቸው ውስጥ ይጠቀሳል ይላሉ ባለሙያው።

በዓሉን በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የእምነቱ ተከታይ ጎበዛዝት በኾታ፣ ወይዛዝርት በጭብጨባ፣ እናቶች በእልልታ፣ አባቶች ደግሞ በእጀባ ኀብር ፈጥረው ፣ ጸዓዳ ለብሰው. ያከብሩታል ነው ያሉት።

በጥምቀት ሰዎች የፈለጉትን ዓይነት ጨርቅ፣ በፈለጉት ዓይነት ስፌት አሰርተው ይለብሳሉ፤ የፈለጉት ዓይነት ባሕላዊ እና ዘመናዊ ማጌጫ ይጠቀማሉ፤ ቀልባቸው የሻተውን ክዋኔም ይይዛሉ ነው የሚሉት።

በከተራም ይሁን በጥምቀት በዓል ሰዎች ኀብረት ፈጥረው በፈለጉት ቋንቋ ቢያቀነቅኑ፣ የፈለጉትን ዝማሬ ቢዘምሩ እና ትዕይንት ቢያሳዩ የሚቃወማቸው አይኖርም ፤ ጠብም አይታሰብም። ይልቁንም ሁሉም ኀብር ፈጥረው በጋራ መዝፈናቸው፤ መጨፈራቸው ይበልጥ በዓሉን ያደምቀዋል እንጅ። በበዓሉ ድንቅ መከባበር እና መተሳሰብ ይንጸባረቅበታል ነው ያሉት ባለሙያው።

ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው የተሰባሰቡ የተለያዩ ብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አንድነት ፈጥረው መጨፈራቸው፣ የየራሳቸውን መገለጫ ክዋኔ መጠቀማቸው የባሕል መወራረስ እንዲኖር ማድረጉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያጠናክረዋል። ባሕልን ያሳድገዋልም ነው ያሉት።

“በጥምቀት በዓል የሚስተዋለው ሰላም፣ አንድነት እና መቻቻል አፍ አውጥቶ ለዓለም ሕዝብ የሚናገረው ሐቅ አለ” ያሉት ደግሞ የታሪክ እና ፎክሎር ምሁር ሙላት ዳኜው ናቸው።

በዓሉ በብሔር ብሔረሰቦች ባሕላዊ አለባበስ በመድመቅ ሰላማዊ በኾነ መልኩ የሚከበር ከመኾኑም ባሻገር ክዋኔዎቹ የሀገር ገጽታን ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ በማስተዋወቅ በኩል ዓይነተኛ ሚና አላቸው። በዓሉ የሕዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክርም ነው ብለዋል።

ወይዛዝርት ጥምቀትን አስታከው ጎበዛዝትን በግጥም ይሸነቁጧቸዋል። ጎበዛዝቱም ግጥምን በግጥም እየመለሱ ይጫወታሉ። በጥምቀት ፍቅር እና ደስታ ከፍ ይላል።

በጥምቀት በዓል በትውልድ ቅብብሎሽ የተሻገረው አንድነት አሁን ድረስ ላይፈታ የተገመደ፣ ላይቆረጥ የጠነከረ መልካም እሴት ነው ብለዋል።

በጥምቀት በዓል ሰዎች ለሰላም ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ። በጥምቀት በዓል ትንንሽ መንገጫገጮች እና የቡድን ጠብ ቢፈጠር እንኳን “በአንተ ተው አንተም ተው” ተብሎ ወዲያውኑ ይፈታሉ። ጥሉ ቂም አይኖርም። ወዲያው ተፈትቶ በዓሉ ይደምቃል እንጂ።

ጥምቀት የሰላም ፣የአንድነት እና የመተሳሰብ ክዋኔዎች ጎልተው የሚወጡበት ነው። ይህም ለኢትዮጵያውያን ተከባብሮ የመኖር ተምሳሌት ነው ብለዋል። ይህ አንድነት እና መቻቻል ደግሞ ወብ ባሕል በመኾኑ ሰርክ ቢተገበር ኢትዮጵያውያን እናተርፍበታለን እንጅ አንከስርበትም ነው ያሉት የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያው ። ጥምቀት አንድነት የሚጸናበት፣ ፍቅር የሚጎለብትበት፣ ሰላምና ደስታ ያለበት በዓል ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባሕር ዳር የጥር እንግዶቿን በወጉ እየተቀበለች በፍቅር እያስተናገደች ነው” ጎሹ እንዳላማው
Next articleየልደትን በዓል በልዩ ወረብ እና ዝማሬ የሚያደምቁ የላሊበላ ካህናት ጥምቀትንም ይደግሙታል።