ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ በድምቀት ለሚከበረው የከተራ በዓል እና ለነገውም የጥምቀት በዓል የታቦታትን መውረጃ እና ማደሪያ ጎዳናዎችን በውኃ እና በሳሙና የማጽዳት መርሐ ግብር ከጠዋት ጀምሮ ተካሂዷል።
በጽዳት እና የአስፋልት መንገዶችን የማጠብ መርሐ ግብሩ ላይ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተው ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ተሳትፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፋት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ጥምቀት በባሕር ዳር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቱሪስቶች ታጅቦ በልዩ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።
በተለይም በውቡ የጣና ሐይቅ እና በስመ ጥሩው የዓባይ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ የሚደረገው ሥርዓተ ጥምቀት የበዓል ልዩ ውበት እየኾነ መምጣቱን አመላክተዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ሁሌም ቢኾን ውብ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ ናት፣ የዛሬው የጽዳት መርሐ ግብር ደግሞ አንድም ለበረከት ነው፣ ከዚያ ሲያልፍም የከተማችንን ውበት ለእንግዶቻችን የበለጠ ለመግለጥ ያለመ ነው ብለዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፤ የበዓሉ ባለቤት የኾኑ ወጣቶች እና ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥርዓቱን በባለቤትነት ወስደው ያከናውናሉ ብለዋል። “በተለይም ወጣቶች የሰላሙ ባለቤት እናንተ ናችሁ፤ የከተማዋ ጠባቂም እናንተው ናችሁ፤ እኛ ደግሞ የማስተባበር ሚናችንን በአግባቡ እንወጣለን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ባሕር ዳር በጥር ሙሽራ ናት” ያሉት ከንቲባው ከጥምቀት ቀጥሎ የቃና ዘገሊላ፣ ሰባሩ ጊዮርጊሥ፣ ጥር ማርያም እና ሌሎችም በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ ገልጸዋል።
የበዓላቱ ባለቤት ሕዝቡ ነው፤ ከሕዝቡ ጋር በጋራ በመኾን ኹነቶች ያለአንዳች እንከን እንዲከበሩ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
ባሕር ዳር በጥር ወር በርካታ ኹነቶችን በድምቀት እያሰናዳች ነው፣ በባሕል እና በወጉ እንግዶችን እየተቀበልን በፍቅር እያስተናገድን ነው ብለዋል።
ለዛሬው የከተራ በዓል እና ለነገው የጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ጊዜው ታከለ ጥር በባሕር ዳር ልዩ ወር ነው ብለዋል። በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓቶች ደምቀው የሚከናወኑበት ወር ነው።
ኹነቶች በተከታታይ የሚካሄዱት እና ቱሪስቶችን በከተማዋ የሚያቆዩም ናቸው ብለዋል። ጥርን በባሕር ዳር በተደራጀ መልኩ መከበር ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመትም ከገና በዓል ዋዜማ ቀድሞ ከአሚኮ ጋር በጋራ በተዘጋጀ “እንቁ ምሥጋና” በሚል መርሐ ግብር ጥርን በባሕር ዳር ተጀምሯል ብለዋል።
ከዚያም ቀጥሎ ባዛሮች፣ አውደ ርዕዮች እና የጥበብ ዝግጅቶችን በማሰናዳት የባሕር ዳር ወዳጆች እና ቱሪስቶች በከተማዋ ያላቸው ቆይታ እንዲያምር መደረጉንም አቶ ጊዜው ተናግረዋል።
ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጣት የትምህርት ከተማ ናት፣ ይህንን በማስመልከትም ማንበብ የሁሉም ሰው ባሕል እንዲኾን የሚያስችል የመጽሐፍት አውደ ርዕይ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
የዛሬው የከተራ በዓል እና ነገ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በድምቀት እና በሰላም እንዲያልፉ፣ ቀጣይ የሚከበሩ ደማቅ የጥር በዓላትም ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች እና የባሕር ዳር ወዳጆች ወደ ከተማዋ በመምጣት የውብ ኹነቶች ታዳሚ እንዲኾኑም አቶ ጊዜው ጋብዘዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!