
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።
በበዓልም ኾነ ከበዓላት ውጭ በአንድነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ነው የምንኖረው ያሉት በጽዳቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ እና የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ መስፍን ጌታሁን የእምነቱ አስተምህሮ እንደሚያዘው ምዕመኑ የሌሎችን እምነት ማክበር ይገባዋል ነው ያሉት።
የደሴ ደብረ መዊ ቅድስት ድንግል ኪዳነ ምህረት እና ቅዱስ መርቆሪዎስ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ እና የበዓሉ አሥተባባሪ መጋቢ ሀዲስ ቤዛ ደሴ ከሌሎች የእምነት ተቋማት የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጽዳት ዘመቻው ላይ መሳተፋቸው አንድነትን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ደሴ እና አካባቢው ሰላም በመኾኑ የአደባባይ በዓላት ያለ ስጋት ይከበራሉ ነው ያሉት።
የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማው ማኅበረሰብ የበኩሉም ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። ከንቲባው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!