ከተራ ምን ማለት ነው?

65

ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከተራን በተመለከተ የትርጓሜ መጽሐፍት መምህር ዘላለም በላይ ከተራ ማለት ከተረ፣ ከበበ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው ይላሉ።
መክበብ፣ ማገድ፣ መከልከል ማለት እንደኾነም የትርጓሜ መምህሩ ይገልጻሉ፡፡

ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው አንጻር ከተራ በሦስት ዓይነት ይገለጻል የሚሉት መምህሩ ይህም ዝግጅታዊ ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ አንደኛው ምሳሌያዊ ሲኾን ይህም ሙሴ እስራኤልን ይዞ ከግብጽ ሲወጣ በያዘው በትር ውኃውን ሲመታው ውኃው ከሁለት ተከፍሎ ጎን ለጎን በመኾን እራሱን ከቦ ወይም ከትሮ በመቆም እስራኤላዊያን በየብስ እና በደረቅ ተሸግረዋል፡፡

ይህ ውኃው እራሱን ከትሮ ወይም ከቦ መቆሙ ለከተራ እንደምሳሌ ኾኖ ይቆጠራል ይላሉ። ሁለተኛው አማናዊ ሲኾን አማናዊ የምንለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚጠመቅበት ወቅት የሚጠመቅበት ውኃ በእሳት ተከቦ እንደነበር መዝሙረ ዳዊት በመዝሙሩ ይናገራል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዩሀንስ በመሄድ አጥምቀኝ ብሎ ሲጠይቀው አንተን ማጥመቅ አይቻለኝም ብሎ ስለ ትህትና ላለማጥመቅ እምቢ ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትህትናህ አንተ ፈጣሪውን ያጠመቀ ተብለህ እኔ ደግሞ በፍጡሩ እጅ የተጠመቀ ተብየ ያንተ ትህትና የኔ ልዕልና ሲነገር ይኖራልና ልታጠምቀኝ ይገባል ብሎ በማዘዙ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንዲሄዱ አደረገ፡፡

ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሲቃረቡ እና ወንዟ ስታየው ሸሸች መዝሙረ ዳዊት በመዝሙሩ ውኃይቱ አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃይቱን እንድትቆም በማዘዝ ለመጠመቅ ወደ ውስጥ ገባ፤ በዚህ ወቅት ውኃው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገባበትን በእሳት እንደከበበው ቅዱስ ያሬድ እሳቱ ውኃውን ከበበው ውኃው የሚሄድበት ጠፋው ተጨነቀ ይላል፡፡

ከዛም ዮሀንስ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራስ ላይ እጁን ሲዘረጋ ውኃው በራሱ ጊዜ እየተነሳ በዮሀንስ እጅ እያለፈ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ፡፡

በዚህ ላይ ውኃው በእሳት ተከቦ መቆሙን ተከተረ እንለዋለን ብለዋል፡፡ ሌላው ዝግጅታዊ የሚባለው ሲኾን ጥምቀትን ለማክበር ወቅቱ የበጋ ወቅት በመኾኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሰውነትን ሊያጠልቅ የሚችል ወይም ተቀድቶ ማንም ሰው እንደፈለገ ሊጠመቅበት የሚችል ውኃ ባለመኖሩ በየቦታው ያሉትን ውኃዎች በእንጨት፣ በድንጋይ እና በተለያዩ ነገሮች እያቆሩ፣ እየከተሩ ያጠራቅማሉ፤ በዚህም ውኃ ማጠራቀማቸው፣ ማከማቸታቸው፣ ማቆማቸው ከተራ ተብሎ በሃይማኖታዊ ስያሜ እንደተሰየመ ነግረውናል፡፡

ከተራ ከጥምቀት አንድ ቀን ቀድሞ ጥር 10 ቀን የሚከበር ሲኾን በቤተክርስቲያን፣ በአማኞች እና በወጣቶች በኩል የሚደረጉ ዝግጅቶች እንዳሉ የሚያብራሩት መምህሩ በወጣቶች ዘንድ የሚደረገው ዝግጅት ውኃውን በመክበብ ወይም በመከተር፣ ወደ ውኃው ታቦታት የሚሄዱበትን መንገድ በማጽዳት፣ ታቦታቱ እና ካህናቱ የሚያርፉባቸው ቦታዎች ላይ ድንኳን በመትከል ቅድመ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ፡፡

መምህሩ እንደነገሩን ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሄደው የሚያድሩበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮሀንስ እንደሄደው ከዛም ወደ ባህሩ ሂደው መጠመቁን በማሰብ እነሱ ባከበሩበት መንገድ ለማክበር የተደረገ ምሳሌ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትህትና ወደ ዮሀንስ እንደሄደው ሁሉ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ሜዳ ላይ በመኾን ክርስቶስ ያሳየውን ክብር በተግባር ለመፈጸም የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ወቅት ወጣቶች ያለማንም ግፊት በራሳቸው ተነሳሽነት በረከት እናገኝበታለን እንከብርበታለን በማለት ታቦታት የሚሄዱበትን መንገድ በማጽዳት፣ ስጋጃ በማንጠፍ፣ የታቦታት ማደሪያውን እና አካባቢውን በሰንደቅ ዓላማዎች ማስዋብ፣ ጸጥታውን የማስተባበር ሥራ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡ የዚህ የበረከት ሥራ ዋጋው ቀላል አይደለም ይላሉ መምህሩ፡፡

ይህን ዝግጅት ያለማንም እረዳት በራሳቸው ተግባብተው እና ተናበው ስለሚሠሩ በዓሉ ያለምንም እንከን እንዲከወን ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህ ላይ የወጣቶች ተሳትፎ እጅግ ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል መምህሩ፡፡

የሚሠሩት ሥራ በረከት የሚያስገኝ፣ ሃይማኖትን፣ ትውፊትን፣ የሀገር ባሕልን የሚያስቀጥል፣ ከሌላ አካባቢ ለሚመጡ ቋንቋውን ለማያውቁ የበዓሉ ታዳሚዎች በትርኢት መልክ የሚያቀርቡት ትዕይንት፣ በስዕል ስለው የሚያሳዩት ምስል በቀላሉ የበዓሉን ክብር የሚያስረዳ ነው ብለዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባለዘንባባዋ ከተማ ልጆች ጎዳናዎችን በማጽዳት ለከተራ እና ጥምቀት በዓል እያዘጋጁ ነው።
Next articleበደሴ ከተማ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ።