
ጎንደር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ተዋህደውባታል፡፡ በተራራዎች መካከል የምትገኘው ጥንታዊት እና ታሪካዊት ከተማ “የአፍሪካ ካሜሎት” የሚል መጠሪያ ተችሯታል፡፡ ጥበብ እንደ ጅረት፣ ውበት እንደ ውኃ ሙላት ፈስሶባታል፡፡ ፍርድ አዋቂ እና ፍትሕ አፍላቂ የኾነችው ከተማ ከመዲናነቷ ሳትጎድል ለሦስት ክፍለ ዘመናት ገደማ መናገሻ ተብላለች፡፡
ከ400 ዓመታት በላይ እንደ ዮርዳኖስ ጥምቀትን በአጀብ እና በታምራት ያሳለፈችው ጎንደር በብዙዎች ዘንድ አይረሴ ትዝታን ሰጥታቸዋለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ጥምቀት ሲነሳ ቀድማ ትዝ የምትላቸው ከተማ ጎንደር ናት፡፡ በደግ ዘመን ሐሴት፤ በፈተና ዘመን ጽናት ጎንደር ጥምቀትን የምታከብርባቸው መሻገሪያ ድልድዮቿ ናቸው፡፡ ጎንደር አመስጋኝ ከተማ ጭምር ናት፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ጎንደር ጥምቀትን በፈተና መካከል ኾናም ቢኾን ከሙላቷ ሳትጎድል አክብራለች፡፡ የጎብኚዎች መዳረሻ የኾነችው ጎንደር ከኮሮና ቫይረስ እስከ የክልሉ የጸጥታ መደፍረስ ድምቀቷን እና ሙላቷን ማጉደል ባይችሉም እንኳን ፈትነዋት አልፈዋል፡፡ ዛሬም ጎንደር ወድቆ እንደ መነሳት ከባድ የሚባለውን ጊዜ በልጆቿ ብስለት እና አስተዋይነት ልትሻገር በተስፋዋ ዳርቻ፣ በመነሳቷ መባቻ ላይ ናት፡፡
የጎንደር ከተማ ጉልላት የኾኑት የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት እና ተጨማሪ ውበት የኾናት የኮሪደር ልማት ጎንደር በጥምቀት ዋዜማ ተመልካቾቿን የምትማርክ ከተማ አድርገዋታል፡፡ በዚህ የመነሳት እና የማንሰራራት ወቅት ላይ ኾነን የምናከብረው የጥምቀት በዓል ልዩ ትርጉም አለው ያሉት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኜው ወራትን የፈጀ የቅድመ ዝግጅት ጊዜ አሳልፈናል ብለዋል፡፡

ጎንደር በተለያዩ ዝግጅቶች ተጠምዳ እንዳሳለፈች ያስታወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘ ገሊላ ሃይማኖታዊ በዓላት በተለመደው መልኩ በድምቀት ይከበራሉ ብለዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የመጡ የጎንደር እንግዶች ጊዜያቸውን በጉብኝት የሚያሳልፉባቸው በርካታ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ መዳረሻዎች ዝግጁ ኾነው እንደሚጠብቋቸው አረጋግጠዋል፡፡
የሆቴል እና ትራንስፖርት አገልግሎት ዝግጅት በበቂ መጠን መኖሩን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንግዶች ምቾት እና ነጻነት ተስምቷቸው እንዲያሳልፉ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የጎንደር ቤተሰብ አስደሳች ዝግጅት እንደሚኖርም አንስተዋል።
ጎንደር ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ እንደኾነች ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለፉት ዘመናት ያሳለፈችው የጨለማ ጊዜ የሚያስቆጭ እንደ ነበር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የብርሃን ዘመናት የተገነቡ አብያተ መንግሥታት በዚህ ዘመን በምሽት የማይጎበኙ ነበሩ ብለዋል፡፡ በከተማዋ ማዕከል ላይ የከተሙት አብያተ መንግሥታት ምሽት በጨለማ የተዋጡ እንደነበሩ ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “ከእንግዲህ ጎንደር ሲመሽ አታንቀላፋም” ብለዋል፡፡
የበዓል ቅድመ ዝግጅቶችን ጨምሮ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በፍጥነት እና በጥራት እንዲሠሩ የሕዝቡ ባለቤትነት ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ ሕልም እና ሃሳባችን ለሕዝብ ይዘን ቀርበን አስረድተናል፤ ሕዝቡም ተረድቶ ተባብሮናል ነው ያሉት። ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
