“ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የአፍሪካ ልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ ናት” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

35

ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ፍላጎታቸው በኾኑ መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦች፣ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ2025 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባኤ አስመልክቶ እያደረገች ያለው ዝግጅት እና ሌሎችም የውይይቱ አጀንዳዎች ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቡድን እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ መደገፍ የሚያስችል ግልጽ የኀላፊነት ተዋረድ መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል። የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ የልማት ግቦቹን አፈጻጸም ለማሻሻል የቀየሰቻቸውን ስትራቴጂዎች አስመልክቶ ለምክትል ዋና ጸሐፊዋ ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ለግቦቹ መሳካት ጠንካራ ትብብር እና ለትግበራው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል። የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የልማት ግቦች እንዲሳኩ እያደረጉት ላለው ጥረት ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት እና አደረጃጀቶች የዘላቂ ልማት ግቦችን እንደ ሀገር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር አጣጥሞ ማስኬድ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በዓለም መድረክ የአፍሪካ ልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መኾኗንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

ኢትዮጵያ እና ተመድ የጋራ ፍላጎታቸው በኾኑ መስኮች ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ በውይይቱ ወቅት መገለጹን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሜቴ ሠብሣቢዎች ገለጹ።
Next article“ከእንግዲህ ጎንደር ሲመሽ አታንቀላፋም”