እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሜቴ ሠብሣቢዎች ገለጹ።

15

ወልድያ: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እና አባላት በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ እና መርሳ ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን ጎብኝተዋል። በሁለቱም አሥተዳደሮች በዋናነት በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተሠሩ ተግባራት በሪፖርት እና በምልከታ ለጎብኝዎች ቀርቧል።

የሀብሩ ወረዳ የግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች እንዲሁም የችግኝ ቅድመዝግጅት በምልከታ ተቃኝተዋል። ከመርሳ ከተማ አሥተዳደር አኳያ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራ፣ የገበያ ማዕከል ግንባታ እና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የጉብኝቱ አካል ነበር።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ከፍያለው ሙላቴ በሀብሩ ያስተዋሏቸው የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ከጸጥታ ችግር አኳያ ሲታዩ የልማት ሥራዎቹ አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከመስኖ ሥራ አኳያ የውኃ ፓምፕ፣ የግብዓት ዋጋ መወደድ እና የአቅርቦት እጥረት የተነሱ ችግሮች በመኾናቸው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ከክልል የሥራ ኀላፊዎች ጋር እንደሚሠሩ አስረድተዋል።

ሁለቱም ወረዳዎች የግብርና ተግባሮቻቸውን በላቀ ሁኔታ ፈጽመዋል ያሉት የቋሚ ኮምቴ ሠብሣቢው ከመብራት እና ከንፁህ መጠጥ ውኃ ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው የቢሮ ኀላፊዎች ጋር በመነጋገር መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

በጅምር ላይ ያሉ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ መፍትሔ ተሰጥቷቸው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚመለከተው የክልል ኀላፊዎች ጋር እንደሚነጋገሩም አረጋግጠዋል።

የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦቱም እንዲሻሻል ጥያቄ መቅረቡን አውስተው መፍትሔ ለመስጠት ይሠራል ነው ያሉት።

የበጀት እና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ ሠብሣቢ ሀናን አብዱ የገጠሩን ማኅበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሠራው ሥራ አበረታች ነው ብለዋል።

በመርሳ ከተማ በኩል የተነሳው የበጀት ጣሪያን ማሻሻል እና የከተማ ሽግግር ጥያቄን መርሳ ከተማ ቢያነሳውም በክልሉ ሌሎች ከተሞችም እየተነሳ በመኾኑ ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚመክሩበት ነው ያስገነዘቡት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የኤች አይቪ ኤድስ እና ተዛማጅ በሽታዎችን ለመቆጣጠር አዲስ የሥራ መመሪያ ተዘጋጀ።
Next article“ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የአፍሪካ ልማት ግቦች እንዲሳኩ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ ናት” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ