
ደሴ: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ እና ተዛማጅ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለማከም በተዘጋጀው መመሪያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል። የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ በዞኑ የበሽታውን ስርጭት ከመከላከል ባለፈ በምርመራ በሽታው በደማቸው የተገኘ ከ17 ሺህ የሚበልጡ ወገኖች መድኃኒት እንዲጀምሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ኤች አይቪ እና ተዛማጅ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለማከም በተዘጋጀው አዲሱ መመሪያ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቅሰው በአዲሱ መመሪያ በሽታውን ለመቆጣጠር በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የኤች አይቪ መከላከል እና መቆጣጠር ኦፊሰር አልማዝ መንግሥቴ በአዲሱ መመሪያ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እና የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ብሎም ለማከም በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት በክልሉ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መጨመሩን ጠቅሰው በሽታውን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለማከም አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በአተገባበሩ ዙሪያም በየደረጃው ምክክር እየተደረገ መኾኑን አንስተው መመሪያው በግንዛቤ ፈጠራ፣ የሕክምና አሰጣጥን በማሻሻል እና በሌሎችም ጉዳዬች ዙሪያ የበሽታውን ስርጭት መግታት የሚያስችል ሰፋ ያለ ማብራሪያ እና ትግበራን ያካተተ ነው ብለዋል።
መመሪያው ወደ ትግበራ ሲገባ በበሽታው መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ከፍተኛ መሻሻል ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ኀላፊው ለዘርፉ መሪዎች እና ባለሙያዎችም ሥልጠና የመስጠት እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እየተከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል።
ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል እና ለማከም የሚሰጡ አገልግሎቶች እየሰፉ ብሎም እየዘመኑ መጥተዋል ያሉት አቶ መልካሙ መመሪያው ተግባራዊ ሲደረግ ተገልጋዮች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ለመመሪያው ተግባራዊነት በየደረጃው የሚገኝ የጤና መሪዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!