
ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ድንቅ ምድር ድንቅ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ሲካሄድ የሰነበተው 16ኛው የአማራ ክልል የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፋት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች መገኛ ሀገር ናት፤ ሕዝቦቿ የራሳቸው የኾነ ድንቅ ባሕል እና የአኗኗር ዘይቤ አላቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በማኅበራዊ፣ በንግድ እና ባሕል ተሳሥረው እና ተባብረው የኖሩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ የአብሮነት እና የአንድነት እሴት ባለቤትም ናቸው ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ባሕል እና ኪነ ጥበብ ዘርፉ፣ የባሕላዊ ጭፈራዎች፣ የሙዚቃዎች፣ የአልባሳት እና የክብረ በዓላት ድምቀት የማንነት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። “ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ብዝኀነትን ጠብቀው በፍቅር እና በሰላም የሚኖሩባት የኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት ሀገር ናት” ነው ያሉት።
ሀገራት በባሕል እና በኪነ ጥበባት ዘርፍ ያላቸውን ሃብት አልምተው የቱሪዝም ገቢያቸውን ጨምረዋል፣ ኢኮኖሚያቸውንም ገንብተዋል ያሉት ሚኒስትሯ እኛም ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ባሕል እና ማንነቶች በመጠቀም ገጽታችንን ከፍ ማድረግ፣ ኢኮኖሚያችንንም ማሳደግ አለብን ብለዋል። ኪነ ጥበብ ኀይል አላት፣ በሀገራችን ላይ ሰላም እና ልማትን ለማስፈን የዘርፉ ባለሙያዎች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
በኪነ ጥበብ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ አንድነትን፣ ልማትን እና መልካም ገጽታን ለመገንባት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተግተው ሊሠሩ እንደሚገባም አመላክተዋል። የኪነ ጥበብ ዘርፉ እንዲያድግ እና ለመልካም ዓላማ እንዲውል የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ከኅዳር/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመላ ሀገሪቱ አካባቢዎች የኪነ ጥበብ ንቅናቄ እየተካሄደ መኾኑንም አንስተዋል። 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሕዝብ በእነዚህ የባሕል እና የኪነ ጥበብ ኹነቶች ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንደኾነም ጠቁመዋል። ዛሬ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ያለው መርሐ ግብርም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተያዘው ንቅናቄ አንዱ አካል መኾኑንም አንስተዋል።
መድረኩ ለገጽታ ግንባታ፣ ለአብሮነት እና ለአንድነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል። ሚኒስትሯ የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫሉ እንዲሳካ ላደረጉ የአማራ ክልል መሪዎችን አመሥግነዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!