
ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዕቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር ፍቅርተ እስጢፋኖስ በክልሉ የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመቆጣጠር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል። በየሳምንቱ በክልሉ ውስጥ ምን አዲስ ክስተት ተፈጠረ? በሚል አሰሳ ይደረጋል ነው ያሉት። በሚደረገው ክትትል ክስተት ሲፈጠር ሰው ላይ የከፋ አደጋ ሳያደርስ በፍጥነት መቆጣጠር መቻሉን ነው የተናገሩት።
በግማሽ ዓመቱ በወባ በሽታ ስርጭት ረገድ ከባለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 65 በመቶ ጨምሯል ነው ያሉት። የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስም በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ መሪዎች በቁርጠኝነት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። ለአብነት በየሳምንቱ ዓርብ “የዓርብ ጠንካራ እጆች ወባን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ከፍተኛ ሥራ እንደተከናወነ ነው የተናገሩት።
በ241 ቀበሌዎች የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት ተደርጓል ያሉት ዳይሬክተሯ ይህም በቅድመ መከላከሉ ረገድ የሚደረገውን ርብርብ ያሳየ ነው ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ በድርቅ እና መሰል አደጋዎች ለተጎዱ ሕጻናት እና አጥቢ እናቶች ለመድረስ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ ጊዜያዊ የተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያዎች ወረርሽኝ እንዳይከሰት የማድረግ ጠንካራ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሙያዎች ቡድንን በመመደብ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።
የወባ በሽታ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ችግር ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጀምሮ እስከ ታች ባሉት መዋቅሮች ድረስ በተደረገው ርብርብ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ተደርጓል ነው ያሉት። የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል አሁንም በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በግማሽ ዓመቱ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የወባ ተጠርጣሪዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 1ሚሊዮን 315ሺህ 970 ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ነው ያሉት። ከዚህ መካከልም 11 ነጥብ 4 በመቶ የሚኾኑት ሕጻናት እና ነፍሰ ጡሮች መኾናቸው ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!