የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን ገለጸ።

26

ደብረ ታቦር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ታቦር ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ናት። ከተማዋ የብዙ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ብሎም ባሕላዊ ትውፊቶችን ያቀፈች ታሪካዊ ከተማ ነች።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት ከተማዋ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ጨምሮ ወርሐ ጥር በሙሉ በአጅባር ሜዳ እና በሌሎችም አካባቢዎች መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ክንዋኔዎች በድምቀት የሚከበሩበት እንደኾነ ገልጸዋል።

ከተማዋ ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት እና በቱሪዝም ዘርፍ አካባቢው እምቅ አቅም ያለው መኾኑን ተናግረዋል። ያሉንን የቱሪዝም ሃብቶች በሚገባ በማሳደግ እና በመግለጥ ከተማዋን እና አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጥምቀት በዓልን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ከንቲባው በቀጣይም ጥር 25 በከተማዋ በፈረስ ጉግስ እና በሌሎች ባሕላዊ ክንዋኔዎች የሚደምቀውን የመርቆርዮስ በዓል በድምቀት ለማክበር እንደ ከተማ በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

የደብረ ታቦር ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እንደዘገበው የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን እና የከተማዋን ጎዳናዎች ጽዱ የማድረግ እና የማመቻቸት ሥራዎችም ተከናውነዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጎንደር የጥምቀት በዓል እንግዶቿን እየተቀበለች ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
Next article“የወባ በሽታ ስርጭት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ጨምሯል” የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት