“ጎንደር የጥምቀት በዓል እንግዶቿን እየተቀበለች ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

23

ጎንደር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከወርሃ መስከረም መባቻ ጀምራ የጥምቀት በዓል ቅድመ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ጎንደር ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው። በጎንደር የሚከበረውን ልዩ የጥምቀት በዓል አስመልክቶ ጎንደር ለከተሙ የብዙኀን መገናኛ ተቋማት መግለጫ የሰጡት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው “ጎንደር ለወራት የዘለቀ የጥምቀት በዓል ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች” ብለዋል።

የጥምቀት በዓል ክብረ በዓል አካል የኾኑ የተለያዩ ዝግጅቶች ከጥር 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄዱ መቆየታቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው 15ኛው ጥምቀትን በጎንደር የባሕል ሳምንት እና 16ኛው የአማራ ክልል የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ዛሬ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ይጠናቀቃል ብለዋል። የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ስኬታማ እንደ ነበር አመላካቾች ናቸውም ብለዋል።

ከነገ ጀምሮ ከተራ፣ ጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ በድምቀት የሚከበሩ የጎንደር ከተማ ተጠባቂ ጌጦች ናቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉን ለመታደም ወደ እናት ጎንደር የገባችሁ እንግዶች ቆይታችሁ ያማረ እና የሠመረ እንደሚኾን እርግጠኞች ነን ብለዋል።

ወደ ጎንደር የመጡ እንግዶች በቆይታቸው “የጎንደር ቤተሰብ መርሐ ግብርን” ጨምሮ በሌሎች ዝግጅቶች ታዳሚዎቻችን ናቸው ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በቂ የሆቴል ዝግጅት እና አገልግሎት መኖሩን ገልጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ በረራዎችን በመፍቀድ ለእንግዶቻችን ምቹ አገልግሎት ስለሰጠልን በጎንደር ሕዝብ ስም ምስጋናዬ ይድረስ ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” ጎንደር ሦስት ነገሮች ተሸምነው የሠሯት ከተማ ናት፣ እምነት፣ መንግሥት እና ኅብረ ብሔራዊነት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን ገለጸ።