
ባሕርዳር: ጥር 09/2017ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት ነገሥታቱ ሥርዓተ መንግሥትና አብያተ መንግሥት አቁመዋል ብለዋል። የእምነት መሪዎች አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን ተክለዋል፣ እነዚህን ሁለቱን ፍለጋ ከመላ ኢትዮጵያና ከውጭ የመጡ ሰዎች ደግሞ ጎንደርን ኅብረ ብሔራዊት ከተማ አድርገዋታል ነው ያሉት።
የጎንደር የጥምቀት በዓል ጎንደር የመንግሥት፣ የቤተ እምነትና የኅብረ ብሔራዊነት ማዕከል በመኾኗ ካቆየቻቸው ዕሴቶቿ አንዱ ነው ብለዋል። ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ አንዳንድ ነገር በአንዳንድ ቦታ ይደምቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጎንደር የሚያከብር ሰው ለጎንደር ትንሣኤ ምስክር ነው ብለዋል። ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ቤተ መንግሥት ይዞታውን ይዞ ታድሷል። ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷል። ከተማው እንደ ሙሽራ እያበበ ነው።
በእውነቱ እነ ዐፄ ፋሲል፣ እነ ዐፄ ቴዎድሮስ ቢመጡ በአድናቆት ከተማቸውን መልሰው መጎብኘታቸው አይቀሬ ነው። የጎንደር ማንሠራራት የኢትዮጵያ ማንሠራራት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል በመልእክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!