ከ9ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ እየተሠራ ነው።

41

ደሴ: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን መሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች እንዲኹም ማኅበረሰቡ ተሳታፊ እንዲኾን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

“የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት እና ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት ለምሥራቅ አማራ ቀጣና ለዞን፣ ለወረዳ መሪዎች እና ለቡድን መሪዎች የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደረጄ ማንደፍሮ የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም እየተከናወነ በሚገኘው ሥራ ውጤት መገኘቱን አመላክተዋል።

በተለይም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለሥራው በተሰጠው ትኩረት ማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ክልሉ ያለውን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም እና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ረገድ የተፈጥሮ ሃብት ልማት መፍትሔ መኾኑን ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊው ያመላከቱት። በክልሉ ያለውን የአፈር አሲዳማነት ለመቀነስም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ አጋዥ በመኾኑ መሪዎች እና የግብርና ባለሙያው በዚህ ዓመት በሚከናወነው ሥራ ማኅበረሰቡ ተሳታፊ እንዲኾን ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንዳለበትም ነው የጠቀሱት።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት በክልሉ ከጥር 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በሰው ኀይል፣ በማልሚያ መሳሪያ ልየታ እና በሌሎችም ተግባራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም በ9ሺህ 87 ተፋሰሶች 366 ሺህ 649 ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማካሄድ መታቀዱን ነው ያመላከቱት። የመድረኩ ተሳታፊ የዞን የሥራ ኀላፊዎችም የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ተመስገን አሠፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” ኢትዮ ቴሌኮም አካታች እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ እየተጋ ነው” ፍሬሕይወት ታምሩ
Next article“ኢትዮጵያዊ ኅብር በጎንደር ሰማይ ስር”