
ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በአፍሪካ የዲጂታል መጻኢ ዕድገት ዙሪያ መክረዋል። ሥራ አሥፈጻሚዋ ፍሬሕይዎት ታምሩ ምክክር ያደረጉት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኩዋይኖር እና የባንኩ የምሥራቅ አፍሪካ ሪጅን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሊያንድር ባሶሌ (ዶ.ር) ከተመራ ከፍተኛ ልዑክ ጋር ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም ከአፍሪካ ግዙፉ የቴሌኮም ኦፕሬተር መኾኑን ገልጸዋል። የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ክፍተትን ለማጥበብ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ እየተጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አፍሪካ ያሉባትን ችግሮች ለማለፍ፣ አዳዲስ ዕድሎችን እና ዘላቂ ልማትን ለመፍጠር ቴክኖሎጂን እና ዲጂታል መፍትሔዎችን መጠቀም እንዳለባት አስገንዝበዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካት እና የአፍሪካ ዲጂታል አቅምን ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውን የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ቁልፍ ዓለም አቀፍ አጋሮችን በመሳብ የበለጸገች ዲጂታል አፍሪካን ራዕይ እውን የማድረግ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኩዋይኖር የኢትዮ ቴሌኮምን ፈጣን ዕድገት እና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እየተጫወተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የኩባንያውን ዲጂታል ኢኒሸቲቭ ለመደገፍ ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!