
አዲስ አበባ: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ “ጥምቀትን በጽዱ አዲስ አበባ” በሚል መሪ መልዕክት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። ጽዳቱ የተካሄደው በጃን ሜዳ የታቦታት ማደሪያ ላይ ነው። የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ አንዳችን የአንዳችን በዓል ደስታችን መኾኑን እና አክብሮታችንን ለመግለጽ ተገኝተናል ብለዋል።
ክርስቶስ ትህትናን ያሳየበት የፍቅር፣ የአንድነት እና የአብሮነት በዓል በመኾኑ ይህንን የበዓሉን ሥፍራ በማጽዳት በዓሉን በጋራ በአንድነት ማክበር ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ወክለው የተገኙት አባ ወልደየስ በዓሉ የፍቅር ነው ብለዋል። ቤተክርስቲያኒቱም ይህንን ስታስተምር ኖራለች ነው ያሉት።
ዋና ዓላማው መተባበርን፣ የጥላቻ እና መለያየትን ከአዕምሮ ማጽዳት ነው ብለዋል። በዓሉን ለማድመቅ እና ቦታውን ለማጽዳት የተገኙትን እና ያስተባበረውን ከተማ አሥተዳደሩንም አመሥግነዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ የጥምቀት በዓል ለዘመናት ሲከበር የቆዬ ትልቅ በዓል መኾኑን ገልጸዋል። ሁሉም የኔ ብሎ የሚያከብረው በዓል መኾኑንም ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩም ጥምቀት በንጹሕ ሥፍራ፣ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጉን ይቀጥላል ነው ያሉት። በዓሉ በአብሮነት እና በሰላም እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!