የንግዱ ማኅበረሰብ ለከተማዋ ልማት እና ሰላም የድርሻውን እንዲወጣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጠየቀ።

20

ደሴ: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ከሚገኙ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በልማት እና መልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል። የውይይቱ ተሳታፊ ሽዊት የሱፍ ከተማዋ ሰላም በመኾኗ ለንግዱ ሥራ አመቺ መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን አጎራባች አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር ጥሬ እቃዎችን እንደየፍላጎታቸው እንዳያመጡ እና እንዳይሸጡ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ይህም የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ እና የዋጋ መጨመር እንዲኖር አድርጓል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት እና ንግዱን በተገቢው መንገድ ለማከናወን በከተማዋ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጋር እንሠራለን ነው ያሉት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ዑስታዝ ሰይድ አህመድ በከተማዋ እየተመዘገቡ ላሉ የልማት ሥራዎች የንግዱ ማኅብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል። ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ዑስታዝ ሰይድ በተለይ የንግድ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ በመንግሥት እና በሕዝብ ተሳትፎ በከተማዋ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም የንግዱ ማኅበረሰብ ለከተማዋ ልማት እና ሰላም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘጋቢ ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪን ጎበኙ።
Next articleማኅበረሰቡ ከአጭበርባሪዎች እንዲጠነቀቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።