የጣና ሐይቅን ህልውና ለመጠበቅ የሚሠራውን ሥራ ሁሉም እንዲደግፍ ተጠየቀ።

29

ባሕር ዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አካባቢ የጣና ሐይቅን ዳርቻ በዘላቂነት ለማልማት እና ለመጠበቅ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው። መድረኩን የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ያዘጋጀው ነው።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ የጣና ሐይቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ጉዳቶች እየደረሡበት መኾኑን ገልጸዋል። የተጀመረውን ሐይቁን የመታደግ እንቅስቃሴ ችግር ፈች በኾነ መዋቅራዊ አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የበርካታ ብዝኀ ሕይዎት ሃብቶች መኖሪያ የኾነውን ሐይቅ በማልማት ብሎም በመጠበቅ ለከተማዋ ከውበት ባሻገር የኢኮኖሚ አቅም እንዲኾን በማድረግ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባልም ነው ያሉት። ጣና ሐይቅ 3ሺህ 156 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ያለው እና የበርካታ ብዝኀ ሕይዎት ሃብቶች መኖሪያ መኾኑን የጣና እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ሥራ አሥኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የእንቦጭ አረም፣ ደለል እና ወደ ሐይቁ የሚለቀቁ ፍሳሾች ለሐይቁ ህልውና ስጋት መኾናቸውንም አስረድተዋል። ኤጀንሲው የሐይቁን ህልውና ለመጠበቅ ማኅበረሰቡን በማስተባበር የሚያከናውነውን እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ በከተማው አካባቢ ያለውን የሐይቁን ህልውና የተመለከተ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል። የሐይቁን ዳርቻ ከየትኛውም የህልውና ስጋት ለመጠበቅ እና ሐይቁን በዘላቂነት ለማልማት ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በምክክር መድረኩ የክልል እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚመለከታቸው ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ እና ምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ የአሳ አስጋሪ ማኅበራት፣ የውኃ አዘል መሬት ተወካዮች፣ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

በመድረኩ የሐይቁን ህልውና ለመታደግ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የቃልኪዳን ስምምነት እንደሚደረግም ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግሮክ – የሰው ሠራሽ አስተውሎት
Next articleየኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪን ጎበኙ።