ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲከወን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።

29

ደብረ ማርቆስ: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2017 ዓ.ም የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል ። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመስገን የጸጥታ ችግሩ የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ተዕጽኖ አሳድሮ መቆየቱን ገልጸዋል። ትምህርት ቤቶች ከማኛውም አይነት የፓለቲካ እንቅስቃሴ ነጻ መኾናቸውን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚታነጽባቸው ናቸው ብለዋል። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲከወን ሁሉም የድርሻውን ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል ።

መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንዲጀምሩ ወላጆች የድርሻቸዉን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት። በዕዉቀት እና በክህሎት የበቃ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል ።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 43 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እያከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል። 17 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አለመጀመራቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት በባለቤትነት በመሥራት የነበሩ ድክመቶችን በማሻሻል የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም የነበሩ ጠንካራ ተግባራትን ማስቀጠል እና በውስንነት የተነሱ ሃሳቦችን ለማሻሻል ዝግጁ መኾናቸዉን ተናግረዋል። ከመማር ማስተማር ባለፈ የተማሪዎችን ዉጤት የተሻለ ለማድረግም የተለያዩ ተግባራት እየተሠሩ መኾኑም ተገልጿዋል ።

በበጀት አመቱ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መኾኑን ከመምሪያው የተገኘዉ መረጃ ይጠቁማል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል የወልድያ ከተማ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ክዋኔ መገለጫ ነው።
Next articleግሮክ – የሰው ሠራሽ አስተውሎት