
ወልድያ: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳደሩ የ2017 ዓ.ም ጥምቀት በዓል በሰላም በሚከበርበት ኹኔታ ላይ ከሦስቱም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ምክክር አድርጓል። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከተማዋ የሁለንተናዊ አብሮነትን ትውፊት ቀድማ የገነባች በመኾኗ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ድባብ እና ክዋኔው ባሻገር ማኅበረሰባዊ ክዋኔ እና ቁርኝትን የሚፈጥር ኾኖ ዘልቋል ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ አውድ ወጥቶ ፖለቲካዊ ስሜት ማንፀባረቂያ ኾኖ የከተማዋን የአብሮነት እሴት እየሸረሸረ መኾኑን ነው ከንቲባው ያስረዱት። ይህን ኹነት በመገደብ ጥምቀትን አባቶቻችን ባሻገሩልን ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ አውድ በማክበር የማስቀጠል ኀላፊነት የትውልዱ ኀላፊነት በመኾኑ ወጣቶች የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል።
በመኾኑም ወጣቱ እንደቀድሞው ሁሉ በባሕላዊ አልባሳት ደምቆ እንዲወጣ እና በበዓሉ ላይ የሚንጸባረቁ የጭፈራ ኹነቶች ነባሩን ትውፊት የሚያስቀጥሉ እንዲኾኑ አደራ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!