
ባሕር ዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን በተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት ወደ ልማት መግባታቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በ166 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ዘንድሮ ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም ተመላክቷል።
በአርጎባ ብሔረሰብ አሥተዳደር ልዩ ወረዳ የቀበሌ 07 ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ ሁሴን በባሕላዊ መስኖ ቢያለሙም በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ አልነበሩም። በአካባቢያቸው ያለው ወንዝ ተጠልፎ ዘመናዊ ካናል በመገንባቱ እና ለመስኖ ልማቱ ምቹ ኹኔታ በመፈጠሩ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በአኹኑ ወቅት ከአንድ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲኹም ስንዴ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው ዘንድሮ በሦስት ዙር ከ80 ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል። የቃሉ ወረዳ ቀበሌ 31 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አሊ በአካባቢያቸው የሚያልፈው የቦርከና ወንዝ ያለ አንዳች ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ መኖሩን አስታውሰዋል።
መንግሥት ወንዙን ጠልፎ በካናል በቂ ውኃ ማሳቸው ድረስ በማምጣቱ በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ሌሎች አትክልቶችን ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል። ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም አልምተው የሚያገኙትን የግብርና ምርት በስፋት ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውንም አመልክተዋል።
በዞኑ በ166 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቅቀው በዚህ ዓመት ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ ኀላፊ ተክሉ ጥላሁን ናቸው። እንደ ኀላፊው ገለጻ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ከ2 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ መንገድ ያለማሉ። ከ7 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ያደርጋሉ።
ቀደም ሲል በባሕላዊ የመስኖ ልማት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰው ዘንድሮ የጀመሩት ዘመናዊ የመስኖ ልማት ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገውም ተናግረዋል። የመስኖ አውታሩ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ ከመኾን ባለፈ ስንዴን ጨምሮ የሰብል ምርታማነታቸውን በማሳደግ ለገበያ መረጋጋት የበኩላቸውን እንዲወጡም ያደርጋል ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በዞኑ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ 17 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!