
ባሕርዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐሙድ ጥር 03/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል። ሀገራቱ በአንካራው ስምምነት መሠረት የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ፀጋ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው ብለዋል። ስምምነቱ የሀገራቱን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል። ቀጣናውን ከማረጋጋት ባለፈ ለዘመናት የነበረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ነው የተናገሩት ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና የመደራደር አቅሟን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያሳየችበት መኾኑንም ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገራት በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዙሪያ የነበራቸውን የቆየ ግንኙነት ለማሳደግ መስማማታቸው ሕዝባቸውን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር ሰላማዊ በኾነ መንገድ ግንኙነቷን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ያሳየችበትና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት የተቀዳጀችበት መኾኑንም አንስተዋል። የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ (ዶ.ር) ሀገራቱ ከዲፕሎማሲ ባሻገር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ መስማማታቸው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን እና ሌሎች ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ስምምነት እንደሚጠቅም አንስተዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ሁለቱ ሀገራት በአንካራ ያደረጉት ስምምነት የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎችን ዕኩይ ተልዕኮ ያከሸፈ መኾኑንም መሪ ተመራማሪው ገልጸዋል።
ሀገራቱ ጥር 03/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙታቸውን ለማደስ ስምምነት ማድረጋቸው በአንካራ የተደረገውን ስምምነት እንዲጸና የሚያደርግ መኾኑን አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!