የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

37

ባሕር ዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በአማራ ክልል በድምቀት ይከበራል። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በርካታ እንግዶች የሚገኙበት የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ደባልቄ በአማራ ክልል ከታኅሣሥ ወር መጨረሻ ጀምሮ በርካታ በዓላት እንደሚከበሩ ገልጸዋል። በዓላቱ በድምቀት እንደሚከበሩም ተናግረዋል። ክልሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሚያስተናግድባቸው ጊዜያቶች መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የጥምቀት በዓል በመላው ኢትዮጵያ የሚከበር መኾኑን የተናገሩት ኀላፊዋ በጎንደር ከተማ ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች ለየት ባለ ድምቀት ይከበራል ነው ያሉት። በበዓሉ በርካታ ጎብኝዎች እንደሚገኙም አንስተዋል። በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት እና ችግር እንዲከበር ልዩ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር እየወጣ የተሻለ ሰላም እየሰፈነበት መኾኑንም አመላክተዋል። የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በዓሉን በሰላም ማክበር እንደሚችሉ ተረድተው እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል። ከአጋር አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስተዋጽኦው ላቅ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት። ለበዓሉ በሰላም መከበር ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ ፖሊስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን በመረዳት ስጋት ሳያድርበት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን መፈጸም እንደሚገባውም አሳስበዋል። በዓልን ምክንያት አድርገው ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊዋ ይህ ድርጊት በሃይማኖት እና በባሕል ነውር የኾነ በሕግም የሚያስጠይቅ ነው ብለዋል።

ለበዓል የሚመጡ እንግዶችን በመልካም የእንግዳ አቀባበል ባሕል መቀበል እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አሽከርካሪዎችም በበዓል ምክንያት የመንገድ መጨናነቅ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ማኅበረሰቡ አጠራጣሪ ጉዳዮችን እና ወንጀሎችን ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል። ፖሊስ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የጸጥታ ኀይሉ ሕዝብ ሰላም ውሎ ሰላም እንዲያድር በትኩረት እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ረዳት ኮሚሽነር መሠረት ደባልቄ ለበዓሉም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደሴ ከተማ የሚገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በከተማዋ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እንደሚደግፉ ገለጹ።
Next articleየኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ነው።