
ደሴ: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በደሴ ከተማ የሚገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በከተማ አሥተዳደሩ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው የከተማው ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረውን እና ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ እየተገነባ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኀይል ማከፋፈያ፤ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን፤ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የኾነበትን የፍሳሽ ማስወገጃ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በደሴ ከተማ አሥተዳደር ያለውን የኤሌክትሪክ ኀይል አቅም ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ ተመላክቷል። በክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እየተሠራ የሚገኘው የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት የከተማዋን ፍሳሽ ቆሻሻ ዳግም ጥቅም ላይ በሚውል መልኩ ለማስወገድ ሚናው ከፍተኛ እንደኾነ ተገልጿል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ከንግዱ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ጎብኝዎች በተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች መደነቃቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይም ከከተማ አሥተዳደሩ ጎን በመቆም የልማቱ አካል እንደሚኾኑም አረጋግጠዋል። ለጎብኝዎች ገለጻ ያደረጉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያው የከተማዋ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የኾነውን የመብራት መቆራረጥ የሚያስቀር መኾኑን ገልጸዋል። በከተማዋ የሚገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች የሚተርፍ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!