
ጎንደር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዕድሜ ዘመን ሙሽራ፣ የሥልጣኔ ቀንዲል፣ ቀደምቷ ከተማ እና መናገሻዋ ጎንደር በወርኃ ጥር ፍጹም ትለያለች። ሃይማኖት፣ ባሕል እና ማንነት የሚንሰላሰሉባት ከተማ ጥምቀት ልደቷ ኾኖ ያልፋል። ጎንደር ላለፉት 400 ዓመታት እንደ ጸሎት ሳታስተጓጉል እና እንደ ግብር ሳታጓድል ስታከብረው የዘለቀችው የጥምቀት በዓል በርካታ እሴትን እና ትውፊትን አጎናጽፏታል። ጥምቀት በጎንደር በልዩ ድባብ በየዓመቱ ይከበራል። የዋዜማዋ ዝግጅቶች የሚያመላክቱት እሱን ነው።
የጥምቀት በዓልን በየዓመቱ በልዩ ዝግጅት ስናከብር ከማኅበራዊ መስተጋብር እና ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ያሉን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ናቸው። ከኮሮና ቫይረስ እስከ ተደጋጋሚ ግጭት እና ጦርነት የቱሪስት መናኾሪያ የነበረችውን ከተማ አቀዛቅዟት ቆይቷል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የዘንድሮውን ጥምቀት ስናከብር ዘርፈ ብዙ ዓላማዎችን ከግምት ውስጥ አስገብተን ነው ብለዋል።
የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና እና የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ቱሪስት እርቋት ለከረመችው ከተማ ተጨማሪ መስህብ እና ውበት ይኾናሉ ብለዋል። የጥምቀት በዓል አንዱ ክስተት የቱሪስት ፍሰት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት በተለየ ጎብኝዎች ወደ ጎንደር ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሌላው ከተማዋ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ስታከብር ታሳቢ ያደረገችው ለመልማት ያላትን ፀጋ በተገቢው ማስተዋወቅ እና አልሚዎችን መሳብ ነው ብለዋል። ጎንደር እና አካባቢው በተለያዩ የምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችል እምቅ አቅም አለ ነው ያሉት። የአካባቢውን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ እና ለመገንባት ጥምቀት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
“ጥምቀት ለጎንደር ከማኅበራዊ ትስስሯ ባሻገር የምጣኔ ሃብት ምንጯም ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉን እያከበርን ለከተማዋ ዳግም መነቃቃት ምክንያት የሚኾኑ የገጽታ ግንባታ ሥራዎች በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!