
ባሕርዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ዘመን እና አዝማናት ሳይጋጩ፤ ዘመናዊነት እና ጥንታዊነት ሳይቃረኑ ከሚንጸባርቁባቸው ቀደምት ከተሞች መካከል ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ጎንደር አንዷ ናት። ጎንደር በረጅሙ እና ውጣ ውረድ በበዛበት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ አስረጂ የምትጠራ ሕያው ምስክር ናት።
የነገሥታት መዲናቸው እና የሊቃውንት ባዕታቸው የነበረችው ጎንደር ተደጋጋሚ ግጭት እና ጦርነት ባደበዘዘው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ውስጥ ዘመን የማይሽረው አሻራ ያላት መናገሻ ናት። ከተማ ኾና እንደ ሀገር የምትጠራ፤ ጥንታዊት ኾና በየዘመኑ የምታበራ የነጻነት፣ የጥበብ፣ የማንነት እና የአብሮነት ቀንዲል ናት ጎንደር።
ጎንደር የጎበኟት በስስት፤ ያልጎበኟት በጉጉት እንደ ተራራዎቿ ለክብሯ ዘብ ይቆማሉ። ጎንደር በሕይዎት ዘመን “ቸር ቢያደርሰኝ አልቀርም” ተብሎ ቀጠሮ ከሚያዝላቸው ውስን ቦታዎች መካከል አንዷ ናት። ጎንደርን ያውም ደግሞ በጥምቀት አለመጎብፕት ያጎድላል ቢባል ማጋነን አይኾንም። ጎንደር ዘዎትር ሙሽራ ብትኾንም በጥምቀት ግን ትለያለች። ጎንደር በጥር በተለይ ደግሞ በጥምቀት እምነት እና ሃይማኖት፤ ባሕል እና ውበት፤ ጀግንነት እና ማንነት ድር እና ማግ ኾነው ይዋሃዱባታል።
ጎንደር ፈተና በገጠማት ዘመን እንኳን በጥምቀት በዓል ከሙላቷ ላለመጉደል ለጎብኝዎቿ ጠብ እርግፍ የምትል ባሕልና ወግ አዋቂ ከተማ ናት። የጥምቀት በዓልን ለማክበር ከመላው ዓለም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ቀደም ብለን ዝግጅት አድርገናል ያሉን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው። ከመስከርም ጀምሮ አንድ ዐቢይ እና ሰባት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዝግጅቶቻችን አጠናቅቀን እንግዶቻችን እየተቀበልን ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ጥምቀትን በጎንደር ስናከብር የምንቆጭባቸውን ታሪኮቻችን ቀይረን፣ ባሕል እና ትውፊቶቻችን አስቀጥለን ነው ብለዋል። የጎንደር አብያተ መንግሥታት እድሳት እና የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዘንድሮው ዓመት የጥምቀት በዓል ገጸ በረከቶች ናቸው ነው ያሉት።
ጥምቀት በጎንደር የአብሮነት ፋይዳው ከፍ ያለ፣ ማኅበራዊ ትስስሩ የተለየ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትርጉሙ የላቀ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የጎንደር ቤተሰብ ለመኾን “ጎንደር በጥር በተለይ ደግሞ በጥምቀት አይቀርም” ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!