“የመስኖ ልማት ሥራ ውጤታማ አድርጎናል” የቃብትያ ሁመራ አርሶ አደሮች

54

ሁመራ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በበጋ መስኖ ልማት በመሠማራት ውጤታማ መኾናቸውን የቃብትያ ሁመራ ወረዳ የሩብ ዓሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የመስኖ ልማት ሥራን ተቀጥሮ ከመሥራት አሁን ላይ ራሱን ችሎ በመሥራት ውጤታማ መኾኑን ወጣት አማኑኤል አሰፋ ገልጿል።

አሁን ላይ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ያስረዳው ወጣት አማኑኤል ጠንክሮ በመሥራቱ ኑሮውን እያሻሻለ እንደኾነ ተናግሯል።

ከዚህ በፊት የራሳቸው መሬት እንደሌላቸው በመግለጽ አሁን ላይ መንግሥት በሰጣቸው መሬት በመስኖ እርሻ ተሠማርተው ቤተሰባቸውን በተሻለ ኹኔታ እየመሩ እንደኾነ የተናገሩት ደግሞ አቶ አጠናው እሸቴ ናቸው።

አርሶ አደሮች የባለሙያዎችን ምክር በመቀበል በተሠማሩበት የመስኖ ልማት ሕይወታቸው እየተሻሻለ መኾኑን የቀበሌው የውኃ ሃብት እና የመስኖ ልማት ባለሙያ ወርቁ ቢምር አስረድተዋል።

ነገር ግን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር እና የቤንዚን እጥረት ለሥራቸው ማነቆ እንደኾነባቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

ከ2016 የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ2017 የምርት ዘመን የዕቅድ አፈጻጸም ብልጫ እንዳለው የገለጹት የዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ እንዳልካቸው አስፋው ናቸው።

በ2017 የምርት ዘመን በዞኑ በአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት 6ሺህ 750 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ5ሺህ 150 ሄክታር በላይ መሬት የለማ ሲኾን ይሄም የዕቅዱ 90 በመቶ እንደኾነ ቡድን መሪው ገልጸዋል።

በዚህም ወደ 4ሺህ100 የሚደርሱ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች መኖራቸውን አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል።

የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለዩኒዬኖች መከፋፈሉን የገለጹት ቡድን መሪው ካለው ፍላጎት አንጻር እየቀረበ ያለው ግብዓት በቂ አለመኾኑን አስረድተዋል።

የተነሱ የግብዓት እጥረቶችን ችግር ለመቅረፍ በተዋረድ እስከ ክልል ድረስ በመነጋገር ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጥምቀት በዓልን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል” ወጣቶች
Next articleለጥምቀት ጎንደር አይቀርም