
ጎንደር፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተለያዩ ማኅበራት እና አደረጃጀቶች የተወጣጡ ወጣቶች ከከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ወጣቶቹም በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጭ መኾናቸውን በውይይት መድረኩ ላይ አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማት ግንባታ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ላሉት ለፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ ለሥራ ኃላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እና ተገቢውን መሥተንግዶ እንዲያገኙ በባለቤትነት ስሜት እንሠራለን ብለዋል ወጣቶቹ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ደግሞ ወጣቶች ለከተማዋ ሰላም በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ወጣቶች በከተማዋ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን በመከላከል የከተማዋን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል አቶ ቻላቸው።
ወጣቶችንም በዚህ ታላቅ በዓል እንግዶችን በመቀበል እና በማስተናገድ፣ የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ፣ ሊፈጸሙ የሚችሉ የስርቆት ወንጀል እና ሌሎች ወንጀሎችን የመከላከል ሥራዎችን በማከናወን ወጣቶች ግንባር ቀደም ኾነው ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!