
ከሚሴ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሸኔ ቡድን አባላት እና አዛዦች መንግሥት እና ሕዝብ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገብተዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከሚሴ ከተማ እና አካባቢው ማኅበረሰብ በድምቀት ተቀብለዋቸዋል።
በቀጠናው የሚንቀሳቀሰው የታጣቂ ቡድኑ ምክትል አዛዥ ኤሌሞ ቂልጡ የሸኔ የጥፋት ቡድኑን ሲቀላቀሉ ለሕዝብ ለመታገል አስበው እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን ቡድኑ ሕዝብን በማሰቃየት እና በመዝረፍ የተሠማራ መኾኑን በመገንዘብ የቀረበልንን የሰላም ጥሪ ተቀብለናል ነው ያሉት። ለሕዝብ እንታገላለን በማለት በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም እንዲመጡም ጠይቀዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ጸሐፊ አሕመድ ጁሀር እስካሁን በቀረበው የሰላም ጥሪ ከ2ዐዐ በላይ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መደረጉን ገልጸዋል። የሰላም ካውንስል አባል አቶ መሐመድ ኡመር በየጊዜው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላም እየመጡ ያሉ አካላት ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሌሎችም የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደ ሰላም እንዲመጡ በሁሉም አካባቢዎች እየሠራን ነው ብለዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አብዱ ጀማል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ምክትል አዛዥ ኤሌሞ ቂልጡ አባላቱ እና አጃቢዎቹ ጋር በሰላም ካውንስሉ በኩል ወደ ሰላም መምጣቱን ገልጸዋል።
እስካሁንም በተደረጉት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች በርካታ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ መደረጉን አሥረድተዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ሕዝብን በማንገላታት እና በትጥቅ ትግል የሚመለስ ጥያቄ የለም ብለዋል። አኹንም በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
