
ደብረ ማርቆስ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም፣ መቻቻል እና አንድነት ከሚገለጥባቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ሰላምን፣ አንድነትን እና ተቻችሎ የመኖርን የቆየ ባሕል ቢፈትኑም ጥምቀትን የመሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት የኢትዮጵያውያን አንድነት ላይፈታ የተገመደ፣ ላይቆረጥ የታሰረ ስለመኾኑ እማኞች ናቸው፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ ቦሌ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የፈለገ ጥበብ ጉባኤ ቤት የብሉያት እና ሐዲሳት መምህር ለዓለም ብርሃኑ እንደ ጥምቀት አይነት ሃይማኖታዊ በዓላት ከመለያየት ይልቅ አንድነት እና ሰላም በተግባር የሚገለጥባቸው ሃብቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ግጭት እና አለመግባባት መቋጫ እንዲያገኝ ወደ ሌሎች ጣትን ከመቀሰር ይልቅ ሁሉም ራሱን ማየት እና መፈተሽ ይገባዋል ነው ያሉት። ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ባሕልን በቅጡ ማውቅ እና መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የዚህ ዘመን መሪዎች የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ስለ መሪነት ያስተማረውን ጥበብ በመላበስ ጥላቻን በማራቅ፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ አርዓያ ኾነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ጥምቀት የአንድነት በዓል መኾኑን የተናገሩት መምህሩ ከመግፋት ይልቅ መደገፍን ፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነት እና መተሳሰብ በተግባር የሚታይበት ሊኾን ይገባል ብለዋል ፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ ባሕሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ሥርዓቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ ቀደምት አባቶቹ ሲያከብሩ የኖሩትን የጥምቀት በዓል ባማረ መልኩ እንዲከበር የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!