” ኪነ ጥበብ ሰላምን ለመገንባት መንገድ ኾኖ የቆየ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

38

ጎንደር: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል 16ተኛው ክልል አቀፍ የባሕል እና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል “ድንቅ ምድር ድንቅ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ ከጥር 07 እስከ ጥር 09/2017 ዓ.ም ይቆያል።

በባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

በክልሉ የሚገኙ የባሕል ማዕከላት እና የባሕል ቡድኖች የክልሉን ባሕል እና ትውፊት የሚያስተዋውቁ ባሕላዊ ክዋኔዎችን አቅርበዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር የባሕል እና ዕሴት ባለቤት መኾኗን ገልጸዋል። ይህንን ጥበብ ወደ ገቢ መቀየር ይገባልም ብለዋል።

ኪነጥበብ አንድነትን የማጠናከሪያ መንገድ ኾኖ አገልግሏል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ይህንን ማስቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጎንደር በምትደምቅበት በጥር ወር ፌስቲቫሉን ማዘጋጀት ለየት የሚያደርገው መኾኑንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ ክልሉ የቱባ ባሕላዊ ትውፊቶች መገኛ፣ የአንድነት እና የአብሮነት መገለጫ የኾኑ ባሕሎች መናኾሪያ መኾኑን ገልጸዋል።

ኪነ ጥበብ የጀግንነት፣ የደስታ እና የሀዘን መግለጫ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ይህንን ማስተዋወቅ ያስፈልጋልም ነው ያሉት። ቱባ ባሕል እንዳይበረዝ መጠበቅ እንደሚገባ የተናገሩት ኀላፊው ባሕል አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ በመኾኑ የገቢ ምንጭ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ቢሮው ባሕልን ለማስተዋወቅ እና ቱባ ባሕልን ጠብቆ ለማቆየት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ፌስቲባሉ የባሕል ትውውቅ፣ የስዕል እና ቲያትር ውድድርን ጨምሮ ሌሎች ባሕልን የሚያስተዋውቁ ትዕይንቶች ተካተውበታል ያሉት ኀላፊው በኪነ ጥበቡ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዕውቅና የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ኪነ ጥበብ ሰላምን ለመገንባት መንገድ ኾኖ የቆየ ነው ብለዋል።የገቢ ምንጭ ይኾን ዘንድ ባሕልን በማስተዋወቅ የሥራ ዕድልን መፍጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ባሕልን በመጠበቅ ለሰላም እና ለኢኮኖሚ ዕድገት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ፌስቲቫሉ በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀ ሲኾን የተለያዩ የጥበብ ውድድሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፦ ቃለልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleየፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ዲጅታላይዝድ አሠራርን መተግበር አስፈላጊ መኾኑን አቶ ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።