
አዲስ አበባ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ባለፉት ስድስት ወራት 10 ቢሊዮን ብር ገቢ ከተለያዩ አገልግሎቶች ለመሰብሰብ ታቅዶ 16 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
ከፓስፖርት ስርጭት አኳያም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ለማሰራጨት ታቅዶ 701 ሺህ ፓስፓርት ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል። ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፋተኛ ስርጭት የተካሄደበት ነው ብለዋል። አገልግሎቱ ከ14 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ መስጠቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ዳዊት 23 ሺህ ለሚኾኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመታወቂያ አገልግሎት መሰጠቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ለ20 ሰዎች የኢትዮጵያዊ ዜግነት ተሰጥቷል ነው ያሉት። ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በስድስት ወራት ሀሰተኛ እና የተጭበረበረ የጉዞ ሰነድ ይዘው አገልግሎት ለማግኘት የሞከሩ 13 ሺህ 322 ዜጎች ተይዘው አስፈላጊው አሥተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።
አገልግሎቱ ቅርንጫፎቹን ለማጠናከር በሁሉም ክልሎች 14 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እየሠራ መኾኑን በመግለጫው ላይ ተመላክቷል። 21 ሺህ 200 ሥራ ፈላጊዎች ተመዝግበው በቅጥር ሂደት ላይ መኾናቸውም ተነስቷል።
ዘጋቢ: ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!