የግል ባለሃብቶችን የሚያበረታታ የልማት ሥነ ምህዳር ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።

20

ደባርቅ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የግል ባላሃብቶችን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አጋር ተቋማትን አወያይቷል። “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት በደባርቅ ከተማ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ፎረምም ተካሂዷል።

የፎረሙ ተሳታፊዎች፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በሀገር ውስጥ ምርት ራስን ለመቻል የኢንዱስትሪ ልማት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል። የሀገርን የልማት እንቅስቃሴ ለማፋጠን በሚደረግ ሂደት የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ሊኾን እንደሚገባ ተጠቅሷል። መንግሥት እና አጋር ተቋማት ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት ብሎም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተነስቷል።

አቶ ርዚቅ ዓሊ የተባሉ በጠጠር እና ጡብ ማምረት ሥራ የተሰማሩ የግል አልሚ በየአካባቢው የኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት መቻሉ የገንዘብ እና የጉልበት ብክነትን ለመቀነስ እና የሀገርን ገጽታ ለመገንባት አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። በዘርፉ ከማስተር ፕላን እና ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል።

አቶ ርዚቅ በቀጣይም መንግሥት ችግሮችን በመፍታት ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሌላው አቶ ጋሻው አውደው የተባሉ በትምህርት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ የግል አልሚ ትምህርት የለውጥ መሣሪያ ነው ብለዋል። አቶ ጋሻው ዘርፉ ሊበረታታ እና ባለሃብቶችም በስፋት ሊሰማሩበት ይገባል ብለዋል።

ተቀራርቦ ለመነጋገር እና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ አቅደው እየሠሩ መኾኑንም የዞኑ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ዘነበ ተናግረዋል። ኀላፊው ከመሠረተ ልማት መሟላት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመብራት፣ የውኃ እና የመንገድ ጥያቄዎችን ለመፍታት እና ምቹ የሥራ ብሎም የልማት ከባቢን ለመፍጠር ከአጋር ተቋማት ጋር እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ላቀው ስለሽ ፎረሙ በዓመቱ ጥሩ የልማት እንቅስቃሴ የነበራቸውን ባለሃብቶች ያበረታታንበት፤ ክፍተት የተስተዋለባቸውን ደግሞ ክፍተቱን ለማጥበብ የተወያየንበት እና የጋራ አቋም የያዝንበት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ጽሕፈት ቤቱ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል። በውይይቱ በከተማዋ የማልማት ፍላጎት ያላቸው የግል ባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙም ጥሪ ቀርቧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመዘርጋት እየሠራች መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።