ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመዘርጋት እየሠራች መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

34

አዲስ አበባ: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአየር ንብረት ለውጥ በግብር እና በምግብ ሥርዓት ላይ የሚያስከትለውን ተግዳሮት ለመቀነስ የሚያስችል ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሥርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ እየሠራች መኾኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ከእርሻ እሰከ ጉርሻ ባለው ሂደት በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ለመዘርጋት ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በፍኖተ ካርታው ግብርና እና ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ 15 የሀገሪቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና የውጭ ሀገር የልማት ድርጅቶች በጥምረት ተግባራዊ የሚያደርጉት ይኾናል ብለዋል።

ማምረት ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ የምርት ብክነት እንዳይኖር፣ የምርት ጥራት እንዳይጓደል ከማድረግ በተጨማሪ ምርትን ወደ ተጠቃሚው ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን የምግብ ደኅንነት ማረጋገጥ እና የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል ተቀዳሚ ተግባር መኾኑን አመላክተዋል። ከማምረት እሰከ ማዕድ ባለው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሀገር ውስጥ ካሉ ባለድርሻ አካላት እና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ ጤናማ እና አምራች ትውልድ ለማፍራት ከእርሻ እሰከ ጉርሻ ጥራቱን የጠበቀ የምግብ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ እንደሀገር በምግብ እጥረት እና በአመጋገብ ሥርዓት የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የተመድ ሰባዊ ርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ.ር) በማደግ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትን የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ የጣለው የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ መኾኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገችው ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በሌማት ቱሩፋት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በአረንጓዴ አሻራ እየተገበረችው ያለው ተግባር ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት መኾኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደር አብያተ መንግሥታትን እድሳት የኮሪደር ልማትን ጎበኙ።
Next articleየግል ባለሃብቶችን የሚያበረታታ የልማት ሥነ ምህዳር ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።