“መንግሥት ነዳጅ ከዓለም ዋጋ እና ከጎረቤት ሀገራትም ዋጋ በታች በከፍተኛ ድጎማ እያቀረበ ነው” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

28

ባሕር ዳር: ጥር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የነዳጅ አቅርቦት እና ድጎማን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከ267 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን አስታውሰዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ ለነዳጅ ድጎማ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ብር በጀት መጽደቁንም ነው ያስገነዘቡት።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግባራ ከተደረገ ወዲህ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለኢኮኖሚው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻል፣ ከልማት አጋሮች ጋር ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም እንዲሻሻል፣ የባንኮች የቁጠባ መጠን እንዲያድግ እና በሁሉም መስኮች ውጤታማ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

የምንዛሬ ተመኑ በገበያ እንዲወሰን መደረጉም ሊመጡ የሚችሉ የዋጋ ጭማሪዎች ኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድሩም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል። በዚህም ነዳጅን ጨምሮ ወሳኝ የሚባሉ ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖራቸው መንግሥት ከፍተኛ ድጎማን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለደመወዝ ጭማሪ፣ ለመድኃኒት፣ ለመሠረታዊ ሸቀጦች፣ ለከተማ እና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ጨምሮ ለሌሎችም በዓመት ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያስከትልም ሪፎርሙ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ኀላፊነት እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት። መንግሥት በሀገሪቷ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር በዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ ነዳጅን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ የሚገዛውን የነዳጅ ምርትም በሀገር ውስጥ በብር እንዲሸጥ ከማድረግ በተጨማሪ በከፍተኛ የመንግሥት ድጎማ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲተላለፍ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት መንግሥት በአጠቃላይ 267 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በዓለም ዋጋ የሚገዛውን የነዳጅ ምርት ከዓለም ዋጋ በታች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራትም ዋጋ በታች በከፍተኛ ድጎማ እያቀረበ መኾኑን ገልጸዋል። እያንዳንዱ ተጠቃሚ በሚገዛው ነዳጅ ላይ የመንግሥት ድጎማ መኖሩንም አመላክተዋል። መንግሥት በሀገሪቱ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን እና በከፍተኛ ድጎማ ለሕዝብ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በኮትሮባንድ ወደ ጎሮቤት ሀገራት እንዳይወጣ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የነዳጅ የግብይት ሥርዓቱን የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በለውጥ ሥራዎች አፈጻጸም ዙሪያ ለመምከር ጎንደር ተገኝተዋል።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደር አብያተ መንግሥታትን እድሳት የኮሪደር ልማትን ጎበኙ።