
ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው የአማራ ክልል ፍርድቤቶችን በኔትወርክ የማገናኘት እና የኦዶቪዥዋል ሥራን ለማከናዎን ውል ወስደዋል። ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ የሲሲቲቪ ውል እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን መፈራረማቸውን ነው የተናገሩት።
ከመግባቢያ ስምምነቱ ጎን ለጎን ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ ፍሬሕይዎት ታምሩ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመሩ የለውጥ እና የሕንፃ ማስፋፊያ እንዲሁም የእድሳት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ዋና ሥራ አሥፈፃሚዋ እንደ ሀገር ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመረው የዲጅታላይዜሽን ሥራ ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአጭር ጊዜ ያሳካቸውን እና እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችንም አድንቀዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው እንደ ኢትዮ – ቴሌኮም ካለ አንጋፋ እና በሀገር ኢኪኖሚ ዕድገት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ካለ ተቋም ጋር አብረው በመሥራታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮ ቴሌኮም በተፈረመው ውል መሠረት በአጭር ጊዜ እና በጥራት አገልግሎቱን እንደሚያቀርብ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የክልሉ ፍርድቤቶች ሥራ በዲጅታላይዜሽን መታገዙ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ሥራው ጊዜ እና ወጭን የሚቆጥብ እንዲሁም የተገልጋዮችን እንግልት በመሠረታዊነት የሚፈታ ነውም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
